ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ “ሕዝቤ ሆይ! በኀጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኀጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አሰበ። እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጡአት። በልብዋ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ ባልቴትም አልሆንም፤ ሐዘንም ከቶ አላይም፤’ ስላለች፥ ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ሐዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ እየጮሁ እያሉ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ ዘይትም፥ የተሰለቀ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሰረገላም፥ ባሪያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፤ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም።” እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ። “ሰማይ ሆይ! ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ! በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።” አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።” በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።
የዮሐንስ ራእይ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ራእይ 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 18:4-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች