መዝሙረ ዳዊት 40
40
ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
1ለድሃና ለምስኪን የሚያስብ ብፁዕ ነው፤
እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል።
2እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥
በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥
በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ አይሰጠውም።
3እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤
መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል።
4እኔስ፥ “አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፤
አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ።
5ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ፦
“መቼ ይሞታል? ስሙስ መቼ ይሻራል?” ይላሉ።
6ከንቱን የሚናገር ይግባና ይይ፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል” ይላል።
ልቡ በላዩ ላይ ኀጢአትን ሰበሰበ፤
ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም፥ በእኔም ላይ ይተባበራል።
7ጠላቶቼም ሁሉ ይጠቃቀሱብኛል፥
በእኔ ላይም ክፋትን ይመክራሉ።
8የበደልን ነገር በእኔ አወጡ።#በዕብራይስጥ ይለያል።
የተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ አይነቃምን?
9ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት፥
እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።
10አንተ ግን አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፥
እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ።
11ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ ዐወቅሁ።
ጠላቶቼ በእኔ ደስ አላላቸውም።
12እኔን ግን ስለ የዋህነቴ ተቀበልኸኝ፥
በፊትህም ለዘለዓለም አጸናኸኝ።
13የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም
ይሁን፥ ይሁን።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 40: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ