መዝሙረ ዳዊት 108
108
ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ፥ ልመናዬን#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “አምላክ ሆይ ምስጋናዬን” ይላል። ቸል አትበል፥
2የዐመፀኛ አፍና የኀጢአተኛ አፍ በላዬ ተላቅቀዋልና።
በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ፤
3በጥል ከበቡኝ፥ በከንቱም ተዋጉኝ።#ዕብ. “ተሰለፉብኝ” ይላል።
4በወደድኋቸው ፋንታ አጣሉኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ።
5በመልካም ፋንታ ክፉን ከፈሉኝ።
በወደድኋቸውም ፋንታ ጠሉኝ።
6በላዩ ኀጢአተኛን ሹም፤
ሰይጣንም በቀኙ ይቁም።
7በሚከራከርም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤
ጸሎቱም በደል ትሁንበት።
8ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤
ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ።
9ልጆቹም ድሃ አደጎች ይሁኑ፥
ሚስቱም መበለት ትሁን።
10ልጆቹም ታውከው ይሰደዱ፥ ይለምኑም፥
ከቤቶቻቸውም ያባርሯቸው።
11ባለ ዕዳም ገንዘቡን ሁሉ ይበርብረው፥
የደከመበትንም ሁሉ ባዕድ ይበዝብዘው።
12የሚረዳውንም አያግኝ፤
ለድሃ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።
13ልጆቹም ይጥፉ፤
በአንዲት ትውልድ ስሙ ትጥፋ።
14የአባቱ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የአባቶቹ” ይላል። ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ፤
የእናቱም ኀጢአት አይደምሰስ።
15በእግዚአብሔርም ፊት ሁልጊዜ ይኑር፤
መታሰቢያውም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “መታሰቢያቸው” ይላል። ከምድር ይጥፋ።
16ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና
ድሃንና ምስኪንንም ሰው አሳዷልና
ልቡም ሰውን ለመግደል የጨከነ ነውና።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ልቡ የተሰበረውንም ለመግደል” ይላል።
17መርገምን መረጣት፥ ወደ እርሱም ትምጣ፤
በረከትንም አልመረጣትም ከእርሱም ትራቅ።
18መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥
እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥
እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች።
19እንደሚለብሰው ልብስ፥
ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ትሁነው።
20ይህ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ
በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው።
21አንተ ግን አቤቱ፥ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ
ምሕረትህን በእኔ ላይ አድርግ፤
ምሕረትህ መልካም ናትና አድነኝ።
22እኔ ድሃና ምስኪን ነኝና፥
ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።
23እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥
እንደ አንበጣም ረገፍሁ።
24ጕልበቶች በጾም ደከሙ፤
ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ።
25እኔም በእነርሱ ዘንድ ተሰደብሁ፤
ባዩኝ ጊዜም ራሳቸውን ነቀነቁ።
26አቤቱ፥ አምላኬ፥ ርዳኝ፥
ስለ ምሕረትህም አድነኝ።
27አቤቱ፥ እጅህ ይህች እንደ ሆነች፥
አንተም ይህችን እንዳደረግህ ይወቁ።
28እነርሱ ይራገማሉ፥ አንተ ግን ባርክ፤
በእኔ ላይ የሚነሡም ይፈሩ፥
ባሪያህ ግን ደስ ይበለው።
29የሚያጣሉኝ እፍረትንና ውርደትን ይልበሱ፤
ኀጢአታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት።
30እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ።
በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ።
31ነፍሴን ከሚከብቡአት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከሚያሳድዱአት” ይላል። ያድን ዘንድ
በእኔ በድሃው ቀኝ ቆሞአልና።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 108: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ