መጽሐፈ ምሳሌ 24
24
1ልጄ ሆይ፥ በክፉ ሰዎች አትቅና፥
ከእነርሱም ጋር መኖርን አትውደድ፤
2ልባቸው ሐሰትን ይማራልና።
ከንፈራቸውም ምቀኝነትን ይናገራልና።
3ቤት በጥበብ ይሠራል፥
በዕውቀትም ይጸናል።
4በዕውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ
ጓዳዎች ይሞላሉ።
5ጠቢብ ሰው ከብርቱ ይሻላል፥
ከታላቅ ርስትም ይልቅ ዕውቀት ያለው ይበልጣል።
6በአስተዳደር ጦርነት ይደረጋል፤
ርዳታም ከምትመክር ልብ ጋር ይሆናል።
7ጥበብና መልካም ዕውቀት በብልሆች በር ትገኛለች፤
ብልሆች ከእግዚአብሔር ቃል አይርቁም።
8ነገር ግን በአንድነት ያስባሉ፥
ሰነፎችንም ድንገት ሞት ያገኛቸዋል።
9ሰነፍ በኀጢአት ይሞታል፤
ነፍሰ ገዳይ ሰውን ርኵሰቱ፥
10በመከራ ቀንና በክፉ ቀን
እስኪያልቅ ድረስ ያረክሰዋል።
11ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤
የሚገደሉትንም መዋረዳቸውን ቸል አትበል።
12እነሆ፥ ይህን አላውቅም ብትል፥
እግዚአብሔር የሁሉን ልብ እንዲያውቅ ዕወቅ።
ለሁሉ እስትንፋስን የፈጠረ እርሱ ሁሉን ያውቃል።
ለሁሉም እንደ ሥራው ይከፍለዋል።
13ልጄ ሆይ፥ ማር ብላ፥
ወለላ ጕሮሮህን ያጣፍጥልህ ዘንድ መልካም ነውና።
14እንዲሁም ጥበብን በሰውነትህ ተማር፥
ብታገኛት ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥ ተስፋህም አይጠፋም።
15ኃጥኣንን ወደ ጻድቃን ቦታ አትውሰድ፤
በሆድህ ጥጋብም አትሳሳት፥
16ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል፥ ሰባት ጊዜም ይነሣል።
ኃጥኣን ግን በክፉ ደዌ ይያዛሉ።
17ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥
በመሰናከሉም አትታበይ።
18እግዚአብሔር ያያልና፥ ደስም አያሰኘውምና፥
ቍጣውን ከእርሱ ይመልሳል።
19ክፋትን በሚያደርጉ ሰዎች ደስ አይበልህ፥
በክፉዎችም አትቅና።
20ዘመኑ ለክፉዎች አይሆንምና#ግሪኩ “ለክፉዎች ዘር አይኖራቸውምና” ይላል።
የኃጥኣንም መብራት ይጠፋልና።
21ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፥
ከእነርሱ ለአንዱ ስንኳ እንቢ አትበል።
22እነርሱ ኀጢአተኞችን ድንገት ይበቀሏቸዋልና፤
የሁለቱንስ ፍርድ ማን ያውቃል?
23የነገሩትን የሚጠብቅ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፥
የሚቀበልም እርሱን ይቀበለዋል።
24ከንጉሥ አንደበት ምንም ሐሰት ይነገራል አይባልም፥
ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም።
25የንጉሥ ቃል ሰይፍ ናት፥
ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ
አንድን አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም።
26ሰይፈ መዓቱ ብትሳል ግን ከዘሮቹ ጋር ሰውን ታጠፋለች፤
የሰውንም አጥንት ትቈረጥማለች።
27በአሞሮች ጫጩት የማይበላ እስኪሆን ድረስ፥
እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች።
28ልጄ ሆይ፥ ነገሬን ፍራ፥ ተቀበለው፥ ንስሓም ግባ፤
ይህንም በእግዚአብሔር ለሚያምኑ ተናግሬ ፈጸምሁ።
29እኔ ከሰው ሁሉ ይልቅ ሰነፍ ነኝና፥
የሰውም ማስተዋል በእኔ ላይ አልነበረምና።
30እግዚአብሔር ጥበብን አስተማረኝ፥
የቅዱሳንንም ዕውቀት ዐወቅሁ።
31ወደ ሰማይ የወጣ፥ የወረደስ ማን ነው?
ነፋስንስ በብብቱ የሰበሰበ ማን ነው?
ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው?
የምድርንስ ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው?
ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን ነው? የልጁስ ስም ማን ነው?
32የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ የጋለ ነው፤
እርሱን ለሚታመኑት ጋሻ ነው።
33እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን
በቃሉ አንዳች አትጨምር።
34ሁለትን ነገር ከአንተ እለምናለሁ፥
ሳልሞትም የሰጠኸኝን ጸጋህን አትከልክለኝ፤
35ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤
ባለጠግነትንና ድህነትንም አትስጠኝ፤
ነገር ግን የሚያስፈልገኝንና የሚበቃኝን ስጠኝ፥
36እጅግ ጠግቤ ሐሰተኛ እንዳልሆን፦
እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤
ድሃም እንዳልሆን፥ እንዳልሰርቅም፥
በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።
37አገልጋይን በጌታው እጅ አሳልፈህ አትስጥ
እንዳይረግምህና እንዳትጠፋ።
38ክፉ ልጅ አባቱን ይረግማል፥
እናቱንም አያመሰግንም።
39ክፉ ልጅ የራሱን ጽድቅ ይፈርዳል
ነገር ግን መውጫውን አይረዳም።
40ክፉ ትውልድ ትዕቢተኛ ዐይን አለው፥
ቅንድቦቹንም ከፍ ከፍ ያደርጋል።
41ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ፥
ጥርሶቹ ሰይፍ፥ መንጋጎቹም መጋዝ የሆኑ ክፉ ትውልድ አለ።#ምዕ. 24 ከቍ. 28 እስከ 41 ያለው በዕብ. ምዕ. 30 ከቍ. 1 እስከ 14 ነው።
42በፍርድ ጊዜ የሰውን ፊት ማፈር መልካም እንዳይደለ ታውቁ ዘንድ
ለጥበበኞች ይህን እነግራችኋለሁ።
43ኃጥኡን፦ “ጻድቅ ነህ” የሚለውን
ወገኖች ይረግሙታል፥ አሕዛብም ይጠሉታል፤
44የሚዘልፉት ግን መታየትን ያሳምራሉ፥
በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች።
45በቀና ነገር የሚመልስ ከንፈር ይሳማል።
46ለመንገድህ ሥራህን አሰናዳ፥
ወደ እርሻ ተዘጋጅ፤
በኋላዬም ተከተልና ቤትህን ሥራ።
47በባልንጀራህ ላይ በሐሰት ምስክር አትሁን፥
በከንፈርህም አትሳት።
48እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥
እንደ ገፋኝም እመልስበታለሁ አትበል።
49በሰነፍ ሰው እርሻ አለፍሁ።
አእምሮ በጐደለውም ሰው የወይን ቦታ ሔድሁ።
50እነሆም፥ በላዩ እሾህ በቅሎበታል፥
ሣሩም ፈጽሞ ደርቋል፥
ምድረ በዳም ሆኖአል፤
የድንጋዩ ቅጥርም ፈርሶአል።
51እኔ ንስሓ ከገባሁ በኋላ
ተግሣጽን እመርጥ ዘንድ ተመለከትሁ።
52ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ታንቀላፋለህ፥
ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ወደ ብብትህ ትሰበስባለህ።
53እንግዲህ ይህን ብታደርግ ድህነት እየቀደመች፥
ችግርም እንደ በጎ ሯጭ#ምዕ. 24 ከቍ. 42 እስከ 53 ያለው በዕብ. ምዕ. 24 ከቍ. 23 እስከ 34 ነው። ትመጣብሃለች።
54ለአልቅት ሦስት የሚዋደዱ ሴቶች ልጆች አሏት።
ሦስቱም የማይጠግቡ ናቸው፤
አራተኛዪቱም በቃኝ ማለት ተሳናት፤
55እነርሱም ሲኦልና የሴት ፍቅር፥
የማትወልድ ማኅፀን፥ ውኃ የማትጠግብየምድር ጕድጓድ፥
በቃኝ የማይሉ ውኃና እሳት ናቸው።
56በአባቱ የሚሥቅ፥
የእናቱንም እርጅና የሚያክፋፋ ዐይንን
የሸለቆ ቍራዎች ያወልቁታል፥
የአሞራዎች ግልገሎችም ይበሉታል።
57ላውቃቸው የማልችል ሦስት ናቸው፥
አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም።
58እነርሱም የሚበርር ንስር ዱካ፥
የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥
የመርከብ ዱካ በባሕር ላይ ሲሄድ፥
የሰውም መንገድ በወጣትነቱ፥
59ሠርታ የምትታጠብ፦
ያደረግሁት አንዳች ክፉ ነገር የለም የምትል
የአመንዝራ ሴት መንገድም እንዲሁ ነው።
60በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥
አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም።
61ባሪያ በነገሠ ጊዜ፥ ሰነፍም እንጀራን በጠገበ ጊዜ፥
62የተጠላች ሴት ቸር ባል ባገኘች ጊዜ፥
ሴት ባሪያም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ።
63በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፤
እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፤
64ገብረ ጕንዳን ኀይል የሌላቸው ናቸው፥
ነገር ግን በመከር ጊዜ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ።
65ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥
ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ።
66አንበጣ ያለ መንግሥት ነው፥
ነገር ግን በአንድ ትእዛዝ አብሮ ይሄዳል።
67እንሽላሊት በእጅ የሚሄድ ደካማ ሲሆን፥
በነገሥታት ቤት ይኖራል።
68መልካም አራማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥
አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፤
69የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥
የማይመለስ፥ እንስሳንም የማይፈራ፤
70ክንፉን እያማታ በእንስቶች ዶሮዎች መካከል የሚሄድ አውራ ዶሮ፤
መንጋን የሚመራ አውራ ፍየል፤
ንጉሥ ሕዝብን ሲገሥጽ።
71ራስህን ለቦዘኔነት ብትሰጥ፥
እጅህንም ለክርክር ብትዘረጋ ቷረዳለህ።
72ወተትን እለብ ቅቤ ይሆንልሃል፥
አፍንጫንም ብትጨምቅ ደም ይወጣል፤
እንዲሁም ነገርን መጐተት ጭቅጭቅንና ቅጣትን ያወጣል።
73የእኔ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ተነገረ።#ዕብ. “እናቱ እርሱን ያስተማረችበት የማሣ ንጉሥ የልሙኤል ቃል” ይላል።
እናቱ ያስተማረችው የንጉሥ ቃል።
74ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሆነ ዐውቀህ ተጠበቅ።
የበኸር ልጄ ሆይ፥ ምንድን ነው? የማኅፀኔ ልጅ ሆይ፥ ምንድን ነው?
የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድን ነው?
ለእግዚአብሔርና ለንጉሥ የማይገባውን አታድርግ።#በግእዝ ብቻ።
75ኋላ እንዳትጸጸት ገንዘብህን፥ ልብህንና ጕልበትህን፥
ለሴቶች አትስጥ።
76ከምክር ጋር ሁሉን አድርግ፥
ከምክር ጋር ወይን ጠጣ፥
መኳንንት ቍጡዎች ናቸው፥
ነገር ግን ወይን አይጠጡ።#ዕብ. “ልሙኤል ሆይ ነገሥታት የወይን ጠጅ ይጠጡ ዘንድ መሳፍንትም ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው ይሉ ዘንድ አይገባም” ይላል።
77ወይንን በመጠጣት ጥበብን እንዳይዘነጓት
ለድሆች ፍርድን ማቃናት አይችሉምና።
78ለኀዘንተኞች ወይንን ስጧቸው፥
የተከዙም ወይንን ይጠጡ።
79ኀዘናቸውን ይረሱ ዘንድ፥
መከራንም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያስቡ።
80አፍህን በእግዚአብሔር ቃል ክፈት፥
ለሕያዋንም ሁሉ ፍረድ።
81አፍህን ክፈት፥ በእውነትም ፍረድ፤
ለድሃና ለምስኪን ፍረድ።#ምዕ. 24 ከቍ. 54 እስከ 81 ያለው በዕብ. ምዕ. 30 ከቍ. 15 እስከ 33 እና ምዕ. 31 ከቍ. 1 እስከ 19 ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 24: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ