ኦሪት ዘኍልቍ 6
6
የናዝራውያን ሕግ
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ወንድ ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ#ዕብ. “የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል” ይላል። ልዩ ስእለት ቢሳል፥ 3ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ከሚያሰክር ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፤ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይንም እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ። 4ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ደረቀው ዘቢብ ድረስ አይብላ።
5“ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ ራሱን አይላጭ፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ ቅዱስ ይሆናል፤ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል።
6“ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። 7ለአምላኩ ያደረገው ብፅዐት በራሱ ላይ ነውና አባቱ፥ ወይም እናቱ፥ ወይም ወንድሙ፥ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው። 8በብፅዐቱ ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና።
9“ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የራሱ ብፅዐት ይረክሳል፤ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው። 10በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 11ካህኑም አንዲቱን ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለተኛዪቱንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ በሬሳም የተነሣ ኀጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፤ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል። 12በስእለቱ ወራትም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይቀደሳል፤ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ስእለቱ#ዕብ. “ናዝራዊነቱ” ይላል። ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ አይቈጠርለትም።
13“የተሳለው ሰው ሕግ ይህ ነው፤ የስእለቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ራሱ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤ ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 14ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥ 15አንድ ሌማትም በዘይት የተለወሰ የስንዴ ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ። 16ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቅርበው። የኀጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል። 17አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል። 18የተሳለውም#ዕብ. “ናዝራዊውም” ይላል። የተሳለውን የራስ ጠጕር በምስክሩ ድንኳን አጠገብ ይላጫል፤ የስእለቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል። 19ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጎቻ፥ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፤ የተሳለውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በባለስእለቱ እጆች ላይ ያኖራቸዋል። 20ካህኑም እነዚህን ሁሉ ቍርባን አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል፤ ይህም የቍርባን ፍርምባና የመባው ወርች ለካህኑ የተቀደሰ ነው፤ ከዚያም በኋላ ባለስእለቱ ወይን ይጠጣል።
21“ስእለቱን የተሳለው የባለስእለቱ፥#ዕብ. “የናዝራዊው” ይላል። እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ስእለቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ስእለቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።”
የካህናት ቡራኬ
22እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 23“ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው፦
24“እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ 25እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም።
26“እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ። 27እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ይጠራሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ