ኦሪት ዘኍልቍ 30
30
ስለ ብፅዐት የተሰጠ ሥርዐት
1ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ነገራቸው፥ “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። 2ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም መሐላን ቢምል፤ ራሱንም ቢለይ፥#“ራሱን ቢለይ” የሚለው በዕብ. የለም። ቃሉን አያርክስ፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ። 3ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባቷ ቤት ሳለች በብላቴንነቷ ጊዜ ራስዋን ብትለይ፥ 4አባቷም ስእለቷንና ራስዋን የለየችበትን ቢሰማ፥ አባቷም ዝም ቢላት፥ ስእለቷ ሁሉ ይጸናል፤ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 5አባቷ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለቷ፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባቷ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል።
6“ባል ያገባች ብትሆን፥ በአንደበቷም እንደ ተናገረች ስለ ራስዋ የተሳለችው ስእለት በራስዋ ላይ ቢሆን፥ 7ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለቷ፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናሉ። 8ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለቷና ራስዋን ያሰረችበት መሐላ አይጸኑም፤ ባልዋ ከልክሎአታልና፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል።
9“ባልዋ የሞተባት ወይም የተፋታች ግን ስእለቷና ራስዋን ያሰረችበት መሐላ ይጸኑባታል። 10ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ 11ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት፥ ባይከለክላትም፥ ስእለቷ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 12ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ስእለቷን ቢከለክላት፥ ስለ ስእለቷ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ ከአፍዋ የወጣው ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከልክሏታል፤ እግዚአብሔርም ያነጻታል።
13“ስእለቷን ሁሉ፥ ነፍስዋንም የሚያዋርደውን የመሐላ ማሰሪያ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፤ ወይም ባልዋ ይከለክለዋል። 14ነገር ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለቷን ሁሉ፥ በእርስዋም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ ያጸናዋል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል። 15ከሰማው በኋላ ግን ቢከለክላት ኀጢአቱን ይሸከማል።” 16እርስዋ በብላቴንነቷ ጊዜ በአባቷ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው ሥርዐት ይህ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 30: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ