ኦሪት ዘኍልቍ 14
14
የሕዝቡ ዐመፅ
1ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንስተው ጮኹ፤ ሕዝቡም ሌሊቱን ሁሉ አለቀሱ። 2የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ፥ “በዚህ ምድረ በዳ ከምንሞት በግብፅ ምድር ሳለን ብንሞት በተሻለን ነበር። 3እግዚአብሔርም በጦርነት እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ለንጥቂያ ይሆናሉ፤ አሁንም ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን?” አሉአቸው።
4እርስ በርሳቸውም፥ “ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ” ተባባሉ። 5ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግንባራቸው ወደቁ። 6ምድሪቱን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ “የሰለልናት ምድር እጅግ በጣም መልካም ናት። 8እግዚአብሔርስ ከመረጠን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል፤ እርስዋንም ይሰጠናል። 9ነገር ግን እናንተ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እኛ እናጠፋቸዋለንና#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “ እንደ እንጀራ ይሆኑልናል” ይላል። የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጊዜአቸው አልፎባቸዋል፤#ዕብ. “ኀይላቸው ደክሞአል” ይላል። እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው” ብለው ተናገሩአቸው። 10ማኅበሩ ሁሉ ግን “በድንጋይ እንውገራቸው” አሉ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ተገለጠ።
ሙሴ ስለ ሕዝቡ እንደ ጸለየ
11እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እኒህ ሕዝብ እስከ መቼ ያስቈጡኛል? በፊታቸውስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምኑብኝም? 12በሞት እቀጣቸዋለሁ፤ አጠፋቸዋለሁም፤ አንተንና የአባትህን ቤት ግን ለታላቅና ከዚህ ለሚበዛ ሕዝብ አደርግሃለሁ” አለው።
13ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ግብፃውያን ይሰማሉ፤ እኒህን ሕዝብ ከእነርሱ በኀይልህ አውጥተኻቸዋልና፤ 14የዚያች ምድር ሰዎች፥ አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብህ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ዐይን በዐይን እንደሚተያይ ተገልጠህላቸዋል። ደመናህም በላያቸው ቆመች። በቀንም በደመና ዐምድ ፥ በሌሊትም በእሳት ዐምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። 15እኒህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ስምህን የሰሙ አሕዛብ፦ 16እግዚአብሔር ‘እነዚህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው’ ብለው ይናገራሉ። 17አሁንም አቤቱ፥ ኀይልህ ይገለጥ፤ እንዲህ ብለህ እንደ ተናገርህ፦ 18እግዚአብሔር መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ጻድቅ፥ አበሳን፥ መተላለፍንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፥ ኀጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኀጢአት እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው። 19እነዚህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የእነዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”
20እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ 21ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝ፤ ስሜም ሕያው ነው፤ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። 22በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ ቃሌንም ስላልሰሙ፥ 23በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእኔ ጋር በዚህ ላሉ መልካምንና ክፉን ለይተው ለማያውቁ ልጆቻቸው፥ የሚያውቀው ለሌለ ለታናሹ ሁሉ ያችን ሀገር እሰጣታለሁ፤ ለጥፋት ያነሳሱኝ ሁሉ አያዩአትም።#ዕብ. ከግእዙና ከግሪክ ሰባ. ሊ. ይለያል። 24ወዳጄ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ በእርሱ ላይ ስለ ሆነና ስለ ተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። 25ዐማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆ ውስጥ ተቀምጠዋል፤ እናንተ ግን ነገ ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።”
የዐመፁት ሕዝብ እንደ ተቀጡ
26እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 27“የሚያጕረመርሙብኝን እኒህን ክፉ ማኅበር እስከ መቼ እታገሣቸዋለሁ? ስለ እናንተ በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤል ልጆች ማጕረምረምን ሰማሁ። 28እንዲህ በላቸው፦ እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 29በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቈጠራችሁ ሁሉ፥ እንደ ቍጥራችሁ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥ 30ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። 31ንጥቂያ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፤ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ይወርሷታል። 32የእናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። 33ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፤ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ። 34ምድሪቱን እንደ ሰለሉባቸው እንደ እነዚያ አርባ ቀኖች ቍጥር ስለ ኀጢአታችሁ ሁሉ አርባው ቀን አርባ ዓመት፥ አንዱ ቀንም አንድ ዓመት ይሁንባችሁ፤ እንግዲህ የቍጣዬን መቅሠፍት ታውቃላችሁ። 35እኔ እግዚአብሔር፦ በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፤ በዚያም ይሞታሉ።”
36ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ስለ እርስዋ በማኅበሩ ሁሉ ፊት አጕረመረሙ። 37ስለዚያችም ምድር ክፉን ነገር ተናገሩ፤ ስለዚያችም ምድር ክፉ የተናገሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ፤ ምድሪቱ ግን መልካም ነበረች።#“ምድሪቱ ግን መልካም ነበረች” የሚለው በግእዙ እንጂ በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 38ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ኖሩ።
ምድሪቱን ለመያዝ የመጀመሪያ ሙከራ
(ዘዳ. 1፥4-46)
39ሙሴም ይህን ነገር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ። ሕዝቡም እጅግ አዘኑ፤ 40በነጋውም ማልደው ተነሡ፤ ወደ ተራራውም ራስ ወጥተው፥ “እነሆ፥ እኛ ከዚህ አለን፤ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን” አሉ። 41ሙሴም አለ፥ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ይህ ለእናንተ መልካም አይደለም። 42እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ። 43ዐማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም።” 44እነርሱ ግን ተደፋፍረው ወደ ተራራው ራስ ወጡ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተንቀሳቀሱም። 45በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ ዐማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፤ መትተዋቸውም እስከ ኤርማ ድረስ አሳደዱአቸው። ወደ ከተማም ተመለሱ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ