የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትን​ቢተ ናሆም 3

3
1ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ሐሰትና ቅሚያ ሞልቶባታል፣ ንጥቂያ ከእርስዋ አያልቅም። 2የአለንጋ ድምፅ፥ የመንኰራኵርም ድምፅ፥ የፈረሶችም ኮቴ፥ የፈጣን ሰረገላም ጩኸት ተሰምቶአል፣ 3ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍም ይንቦገቦጋል፥ ጦርም ይብለጨለጫል፣ የተገደሉትም ይበዛሉ፥ በድኖችም በክምር ይከመራሉ፥ ሬሳቸውም አይቈጠርም፣ በሬሳቸውም ይሰናከላሉ። 4ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፣ እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች። 5እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ልብስሽን በፊትሽ እገልጣለሁ፣ ኅፍረተ ሥጋሽንም ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ። 6ርኵሰትንም በላይሽ እጥላለሁ፥ እንቅሽማለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ። 7የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ፦ ነነዌ ባድማ ሆናለች፣ የሚያለቅስላትስ ማን ነው? የሚያጽናናትንስ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል።
8አንቺ በመስኖች መካከል ከተቀመጠችው፥ ውኃም በዙሪያዋ ከነበራት፥ ምሽግዋም ባሕር ከነበረ፥ ቅጥርዋም በባሕር ውስጥ ከነበረ ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን? 9ኢትዮጵያና ግብጽ የማይቈጠር ኃይልዋ ነበሩ፣ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ። 10እርስዋ ግን ተማርካ ፈለሰች፣ ሕፃናቶችዋ በመንገድ ሁሉ ራስ ላይ ተፈጠፈጡ፣ በከበርቴዎችዋም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ታላላቆችዋም ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ። 11አንቺም ትሰክሪአለሽ ወራዳም ትሆኛለሽ፣ አንቺ ደግሞ ከጠላት የተነሣ መጠጊያን ትፈልጊአለሽ። 12አምባሽ ሁሉ የመጀመሪያውን የበሰለ ፍሬ እንደ ያዙ እንደ በለስ ዛፎች ነው፣ ቢወዛወዝ በሚበላው አፍ ውስጥ ይወድቃል። 13እነሆ፥ በመካከልሽ ያሉ ሕዝብሽ ሴቶች ናቸው፣ የአገርሽ በሮች ለጠላቶችሽ ፈጽሞ ተከፍተዋል፥ እሳትም መወርወሪያዎችህን በልቶአል። 14ከብበው ያስጨንቁሻልና ውኃን ቅጂ፣ አምባሽን አጠንክሪ፣ ወደ ጭቃ ገብተሽ እርገጪ፣ የጡብን መሠሪያ ያዢ። 15በዚያ እሳት ይበላሻል፥ ሰይፍ ያጠፋሻል፥ እንደ ደጎብያ ይበላሻል፣ እንደ ደጎብያ ብዢ፥ እንደ አንበጣም ተባዢ። 16ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ አበዛሽ፣ ደጎብያ ተዘረጋ፥ በረረም። 17በአንቺ ዘንድ ዘውድ የጫኑት እንደ አንበጣ፥ አለቆችሽም እንደሚንቀሳቀሱ ኩብኩባዎች ናቸው፣ በብርድ ቀን በቅጥር ውስጥ ይቀመጣሉ፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ያኰበኵባሉ፣ ስፍራቸው በየት እንደ ሆነ አይታወቅም። 18የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ እረኞችህ አንቀላፍተዋል፣ መኳንንቶችህም ዐርፈዋል፣ ሕዝብህም በተራሮች ላይ ተበትኖአል፥ የሚሰበስበውም የለም። 19ስብራትህ አይፈወስም፥ ቁስልህም ክፉ ነው፣ ወሬህንም የሚሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፣ ክፋትህ ሁልጊዜ ያላለፈችበት ሰው ማን ነውና?

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ