የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትን​ቢተ ናሆም 2

2
1የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፣ ምሽግን ጠብቅ፥ መንገድንም ሰልል፣ ወገብህን አጽና፥ ኃይልህንም እጅግ አበርታ። 2ዘራፊዎች ዘርፈዋቸዋልና፥ የወይናቸውንም አረግ አጥፍተዋልና እግዚአብሔር የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል። 3የኃያላኑ ጋሻ ቀልቶአል፥ ጽኑዓንም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱም በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፣ የጦሩም ሶመያ ይወዛወዛል። 4ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይነጕዳሉ፥ አደባባይም ይጋጫሉ፣ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይከንፋሉ። 5መሳፍንቱን ያስባል፣ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፣ ፈጥነው በቅጥርዋ ላይ ይወጣሉ፥ መጠጊያም ተዘጋጀለት። 6የወንዞቹም መዝጊያዎች ተከፈቱ፥ የንጉሡ ቤትም ቀለጠች። 7ንግሥት ተገለጠች፥ ተማረከችም፥ ሴቶች ባሪያዎችዋም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ ዋይ ዋይ ይላሉ።
8ነነዌ ግን ከዱሮ ዘመን ጀምራ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፣ አሁን ግን ይሸሻሉ፣ እነርሱም፦ ቁሙ፥ ቁሙ ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም። 9መዝገብዋ መጨረሻ የለውምና፥ የከበረውም የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቈጠርምና ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ። 10ባዶና ባድማ ምድረ በዳም ሆናለች፣ ልብ ቀልጦአል፥ ጕልበቶችም ተብረክርከዋል፣ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሰዎችም ሁሉ ፊት ጠቍሮአል። 11የአንበሾችም መደብ፥ የአንበሾችም ደቦል የሚሰማራበት፥ አንበሳውና አንበሳይቱ ግልገሉም ሳይፈሩ የሚሄዱት ስፍራ ወዴት ነው? 12አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል። 13እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ሰረገሎችዋንም አቃጥዬ አጤሳለሁ፥ ሰይፍም የአንበሳ ደቦሎችሽን ይበላቸዋል፣ ንጥቂያሽንም ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልክተኞችሽን ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ አይሰማም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ