ከዐሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው፤ ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። የፋሲካን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ?” አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “ወደ ከተማ ሂዱ፤ ማድጋ ውኀ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ተከተሉት። የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል፤’ በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤በዚያም አሰናዱልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጡ፤ ወደከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል፤” አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና “እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም፤” አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። ኢየሱስም “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛዉን እመታለሁ፤ በጎችም ይበተናሉ፤’ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ “ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም፤” አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
የማርቆስ ወንጌል 14 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 14:10-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች