የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 28

28
የኢየሱስ ከሙታን መነሣት
(ማር. 16፥1-8ሉቃ. 24፥1-12ዮሐ. 20፥1-10)
1በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 2እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። 3መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። 4ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፤ እንደ ሞቱም ሆኑ። 5መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ 6እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና፤ በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። 7ፈጥናችሁም ሂዱና ‘ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ፤’ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። 8እነሆም ነገርኋችሁ።” በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ። 9እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና “ደስ ይበላችሁ፤” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 10በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፤ በዚያም ያዩኛል፤” አላቸው።
11ሲሄዱም ሳሉ እነሆ፥ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ። 12ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው 13“እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት” በሉ። 14ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን፤ እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን፤” አሉአቸው። 15እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲያስተምሩ እንዳዘዛቸው
(ማር. 16፥14-18ሉቃ. 24፥36-49ዮሐ. 20፥19-23የሐዋ. 1፥6-8)
16ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፤ 17ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ። 18ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። 19-20እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም፥ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 28