የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 26:44-75

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 26:44-75 አማ2000

ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፤ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል፤” አላቸው። ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት፤” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን፤” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን ነገር መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ፤ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት። እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ ‘እንደዚህ ሊሆን ይገባል፤’ የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው፤” አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙም፤ ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም። በኋላም ሁለት ቀርበው “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ፤’ ብሎአል፤” አሉ። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ “ተሳድቦአል፤ እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ። እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፤ ሌሎችም በጥፊ መትተው “ክርስቶስ ሆይ! በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን፤” አሉ። ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ “አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ፤” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቀውም፤” ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት “ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ፤” አለች። ዳግመኛም ሲምል “ሰውየውን አላውቀውም፤” ብሎ ካደ። ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን “አነጋገርህ ይገልጥሃልና፥ በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ፤” አሉት። በዚያን ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም፤” ብሎ ራሱን ሊረግምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች