የማቴዎስ ወንጌል 2
2
የሰብአ ሰገል መምጣት
1-2ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፤ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ 4የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። 5-6እነርሱም
“ ‘አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥
ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤
ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና’
ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው” አሉት።
7ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ። 8ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። 9እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። 10ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። 11ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። 12ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ።
ሕፃኑ ወደ ግብጽ እንደሸሸ
13እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። 14-15እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።
ስለ ሕፃናት መገደል
16ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። 17ያን ጊዜ እንዲህ ሲል በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ፤
18“ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤
ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤
መጽናናትም አልወደደችም፤ የሉምና።”
የሄሮድስ ምሞትና የሕፃኑ ከግብጽ መመለስ
19ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ 20“የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለ። 21እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። 22በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ 23በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ