ወደ ምድርም በወረዱ ጊዜ ጋኔን ያደረበት ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፤ ልብሱንም ከጣለ ብዙ ዘመን ሆኖት ነበር፤ በመቃብር ብቻ ይኖር ነበር እንጂ ወደ ቤት አይገባም ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስንም ባየው ጊዜ ጮኸ፤ ሮጦም ሰገደለት፤ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ካንተ ጋር ምን አለኝ?” እያለም በታላቅ ቃል ጮኸ፤ እንዳያሠቃየውም ማለደው። ክፉውን ጋኔን ከዚያ ሰው ላይ እንዲወጣ ያዝዘው ነበርና፤ ዘወትርም አእምሮዉን ያሳጣው ነበርና፤ ብላቴኖችም በእግር ብረት አስረው ይጠብቁት ነበር፤ እግር ብረቱንም ይሰብር ነበር፤ ጋኔኑም በምድረ በዳ ያዞረው ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ስምህ ማነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም፥ “ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው፤ ብዙ አጋንንት ይዘውት ነበርና። ወደ ጥልቁም ይገቡ ዘንድ እንዳይሰድዳቸው ማለዱት። በዚያም ብዙ የእሪያ መንጋ በተራራ ላይ ተሰማርቶ ነበር፤ ወደ እሪያዎችም እንዲገቡባቸው ይፈቅድላቸው ዘንድ ማለዱት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። እነዚያ አጋንንትም ከዚያ ሰው ላይ ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፤ የእሪያዎችም መንጋ አብደው ከገደሉ ወደ ባሕር ጠልቀው ሞቱ። እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው ሄዱና ገብተው በከተማዉና በመንደሩ አወሩ። ሰዎችም የሆነውን ያዩ ዘንድ ወጡ፤ ሄደውም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ በደረሱ ጊዜ አጋንንት የወጡለትን ያን ሰው አእምሮዉ ተመልሶለት ልብሱን ለብሶ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። ያዩትም ሰዎች ጋኔን አድሮበት የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ ነገሩአቸው። በጌርጌሴኖንም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከእነርሱ ዘንድ እንዲሄድላቸው ማለዱት፤ ጽኑ ፍርሀት ይዞአቸዋልና፤ ጌታችን ኢየሱስም በታንኳ ሆኖ ተመለሰ። ያም አጋንንት የወጡለት ሰው ከእርሱ ጋር ይሄድ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስን ማለደው፤ እርሱ ግን፥ “ወደ ቤትህ ተመልሰህ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላቅ ነገር ሁሉ ተናገር” ብሎ አሰናበተው። እርሱም ሄዶ በከተማዉ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ያደረገለትን ሁሉ ተናገረ።
የሉቃስ ወንጌል 8 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 8:27-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች