እርሱ ግን ወደ ምድረ በዳ እየወጣ ይጸልይ ነበር። ከዚህም በኋላ፥ ከዕለታት በአንድ ቀን ሲያስተምራቸው እንዲህ ሆነ፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች፥ ከኢየሩሳሌምም የመጡ ፈሪሳውያንና የኦሪት መምህራን ነበሩ፤ እርሱም ይፈውስ ዘንድ የእግዚአብሔር ኀይል ነበረ። እነሆ፥ ሰዎች በአልጋ ተሸክመው ሽባ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እንዲፈውሰውም ወደ እርሱ ሊያስገቡት ወደዱ። ሰውም ተጨናንቆ ነበርና የሚያስገቡበት አጡ፤ ወደ ሰገነትም ወጡ፤ ጣራውንም አፍርሰው ወደ ቤቱ ውስጥ በጌታችን በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት። እምነታቸውንም አይቶ ያን ሰው፥ “ኀጢአትህ ተሰረየልህ” አለው። ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “የሚሳደብ ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ማስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር። ጌታችን ኢየሱስም የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “በልባችሁ ምን ታስባላችሁ? ኀጢአትህ ተሰረየልህ ከማለትና ተነሥተህ ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ ያን ሽባ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ ብዬሃለሁ” አለው። ያንጊዜም ተነሥቶ ተኝቶበት የነበረውን አልጋ በፊታቸው ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። ሁሉም ተደነቁ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፤ እጅግም እየፈሩ፥ “ዛሬ ድንቅ ነገር አየን” አሉ። ከዚህም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ ሰው በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየና፥ “ተከተለኝ” አለው። ሁሉንም ተወና ተነሥቶ ተከተለው። ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ብዙ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከእርሱም ጋር ለምሳ ተቀምጠው የነበሩ ቀራጮችና ኀጢአተኞች፥ ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ። ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “ከቀራጮችና ከኃጥኣን ጋር ለምን ትበላላችሁ? ትጠጡማላችሁ?” ብለው በደቀ መዛሙርቱ ላይ አንጐራጐሩ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ባለ መድኀኒትን በሽተኞች እንጂ ጤነኞች አይሹትም። ኃጥኣንን ወደ ንስሓ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”
የሉቃስ ወንጌል 5 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 5:16-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች