ስለ ቤተ መቅደስም ድንጋዩ ያማረ ነው፥ አሠራሩም ያጌጠ ነው የሚሉት ነበሩ። እንዲህም አላቸው፥ “ይህን ታያላችሁን? በእዚህ ቦታ ድንጋይ በድንጋይ ላይ የማይተውበትና ሳይፈርስ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል።” እነርሱም፥ “መምህር ሆይ፥ ይህ መቼ ይደረጋል? ይህስ የሚሆንበት ጊዜው፥ ምልክቱስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ፤ ጊዜውም ደርሶአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና እንዳያስቱአችሁ ተጠንቀቁ፤ እነርሱንም ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርነትንና ጠብን፥ ክርክርንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን ወዲያው የሚፈጸም አይደለም።” እንዲህም አላቸው፥ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ነገሥታትም በነገሥታት ላይ ይነሣሉ። በየሀገሩ ታላቅ የምድር መነዋወጥና ራብ፥ በሰውም ላይ በሽታና ፍርሀት ይመጣል፤ በሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ አስቀድሞ ይይዙአችኋል፤ ወደ አደባባዮችም ይወስዱአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ያስሩአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ መሳፍንት ይወስዱአችኋል። ይህም በእነርሱ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል። ዕወቁ፤ የምትናገሩትንም በልባችሁ አታስቡ። በእናንተ ላይ የሚነሡ ሊመልሱላችሁና ሊከራከሯችሁ እንዳይችሉ እኔ አፍንና ጥበብን እሰጣችኋለሁ። ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ወዳጆቻችሁና ባልንጀሮቻችሁ አሳልፈው ይሰጡአችኋል። ሁሉም ስለ ስሜ ይጠሉአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም። ነገር ግን ከራስ ጠጕራችሁ አንዲቱ እንኳ አትጠፋም። በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ። “ኢየሩሳሌምን ጭፍሮች ከብበዋት ባያችሁ ጊዜ ጥፋቷ እንደ ደረሰ ዕወቁ። ያንጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ፤ በመካከልዋ ያሉም ከእርስዋ ይውጡ፤ በአውራጃዎችዋ ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ። በእርስዋ ላይ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እርስዋን የሚበቀሉበት ጊዜዋ ነውና። ነገር ግን በዚያ ወራት ለፀነሱና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ በምድር ላይ ጽኑ መከራ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ መቅሠፍት ይሆናልና። በሰይፍ ስለት ይወድቃሉ፤ በአሕዛብም ሁሉ ይማረካሉ፤ የአሕዛብ ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ አሕዛብ ኢየሩሳሌምን ይረግጡአታል። “በፀሐይና በጨረቃ፥ በከዋክብትም ላይ ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ይጨነቃሉ፤ ከባሕሩና ከሞገዱ ድምፅ የተነሣም ይሸበራሉ። በዓለም ላይ ከሚመጣው ፍርሀትና ሽብር የተነሣም የሰዎች ነፍስ ትዝላለች፤ ያንጊዜ የሰማያት ኀይል ይናወጣልና። ያንጊዜም በሰማይ ደመና፥ በፍጹም ኀይልና ክብር ሲመጣ የሰውን ልጅ ያዩታል። ይህም ሁሉ በሆነ ጊዜ ወደ ላይ አቅንታችሁ ተመልከቱ፤ ራሳችሁንም አንሡ፤ የሚያድናችሁ መጥቶአልና።” ምሳሌም መስሎ እንዲህ አላቸው፥ “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ። ለምልመውም ያያችኋቸው እንደ ሆነ መከር እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እናንተም ይህ እንደ ሆነ ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ደረሰች ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪደረግ ድረስ ይህቺ ትውልድ አታልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፥ በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች። በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደ ተዘረጋች ወጥመድ ትደርሳለችና። እንግዲህ ከዚህ ከሚመጣው ሁሉ በጸሎታችሁ ማምለጥ እንድትችሉ፥ በሰው ልጅ ፊትም እንድትቆሙ ሁልጊዜ ትጉ።” ቀን ቀን በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሌሊት ግን ወጥቶ ደብረ ዘይት በሚባለው ተራራ ያድር ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ቃሉን ሊሰሙ እርሱ ወዳለበት ወደ መቅደስ ማልደው ይሄዱ ነበር።
የሉቃስ ወንጌል 21 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 21:5-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች