ስለ ቤተ መቅደስም ድንጋዩ ያማረ ነው፥ አሠራሩም ያጌጠ ነው የሚሉት ነበሩ። እንዲህም አላቸው፥ “ይህን ታያላችሁን? በእዚህ ቦታ ድንጋይ በድንጋይ ላይ የማይተውበትና ሳይፈርስ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል።” እነርሱም፥ “መምህር ሆይ፥ ይህ መቼ ይደረጋል? ይህስ የሚሆንበት ጊዜው፥ ምልክቱስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ፤ ጊዜውም ደርሶአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና እንዳያስቱአችሁ ተጠንቀቁ፤ እነርሱንም ተከትላችሁ አትሂዱ። ጦርነትንና ጠብን፥ ክርክርንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን ወዲያው የሚፈጸም አይደለም።” እንዲህም አላቸው፥ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ነገሥታትም በነገሥታት ላይ ይነሣሉ። በየሀገሩ ታላቅ የምድር መነዋወጥና ራብ፥ በሰውም ላይ በሽታና ፍርሀት ይመጣል፤ በሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። ከዚህም ሁሉ አስቀድሞ ይይዙአችኋል፤ ወደ አደባባዮችም ይወስዱአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ያስሩአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ መሳፍንት ይወስዱአችኋል። ይህም በእነርሱ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል። ዕወቁ፤ የምትናገሩትንም በልባችሁ አታስቡ። በእናንተ ላይ የሚነሡ ሊመልሱላችሁና ሊከራከሯችሁ እንዳይችሉ እኔ አፍንና ጥበብን እሰጣችኋለሁ። ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ወዳጆቻችሁና ባልንጀሮቻችሁ አሳልፈው ይሰጡአችኋል። ሁሉም ስለ ስሜ ይጠሉአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም። ነገር ግን ከራስ ጠጕራችሁ አንዲቱ እንኳ አትጠፋም። በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ። “ኢየሩሳሌምን ጭፍሮች ከብበዋት ባያችሁ ጊዜ ጥፋቷ እንደ ደረሰ ዕወቁ። ያንጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ፤ በመካከልዋ ያሉም ከእርስዋ ይውጡ፤ በአውራጃዎችዋ ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ። በእርስዋ ላይ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እርስዋን የሚበቀሉበት ጊዜዋ ነውና። ነገር ግን በዚያ ወራት ለፀነሱና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ በምድር ላይ ጽኑ መከራ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ መቅሠፍት ይሆናልና። በሰይፍ ስለት ይወድቃሉ፤ በአሕዛብም ሁሉ ይማረካሉ፤ የአሕዛብ ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ አሕዛብ ኢየሩሳሌምን ይረግጡአታል።
የሉቃስ ወንጌል 21 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 21:5-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች