ከእነርሱም ተለይተው ከሄዱ በኋላ፥ የሚጠባበቁትን አዘጋጁለት፤ በአነጋገሩም ያስቱት ዘንድ ወደ መኳንንትና ወደ መሳፍንት አሳልፈው ሊሰጡት ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰላዮችን ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም እንዲህ ብለው ጠየቁት፥ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነት እንደምትናገርና እንደምታስተምር፥ ፊት አይተህም እንደማታዳላ፥ የእግዚአብሔርንም መንገድ በቀጥታ እንደምታስተምር እናውቃለን። ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል? ወይስ አይገባም?” ተንኰላቸውንም ዐውቆ፥ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? ገንዘቡን አሳዩኝ” አላቸው። አምጥተውም አሳዩት፤ “መልኩ፥ ጽሕፈቱስ የማነው?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የቄሣር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፥ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። በሕዝቡም ሁሉ ፊት በአነጋገሩ ማሳሳት ተሳናቸው፤ መልሱንም አድንቀው ዝም አሉ። “ሙታን አይነሡም” ከሚሉ ከሰዱቃውያንም አንዳንድ ሰዎች ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም እንዲህ ብለው ጠየቁት፥ “መምህር ሆይ፥ ሙሴ፦ ‘ወንድሙ ልጅ ሳይወልድ ሚስቱን ትቶ የሞተበት ሰው ቢኖር ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ’ ሲል ጽፎልናል። እንግዲህ ከእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ታላቁ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ። እንደዚሁም ሁለተኛው አገባት፤ እርሱም ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሦስተኛውም አገባት፤ እንዲሁም ሰባቱ ሁሉ አገቡአት፤ ልጅ ሳይወልዱም ሞቱ። ከሁሉም በኋላ ያቺ ሴት ሞተች። እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ከእነርሱ ለማንኛው ሚስት ትሆናለች? ሰባቱም ሁሉ አግብተዋት ነበርና።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፥ ይጋባሉም፤ ይወልዳሉ፥ ይዋለዳሉም። ያን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ሊወርሱ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም፤ አይጋቡም። እንግዲህ ወዲህ ሞት የለባቸውም፤ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ናቸው እንጂ፤ የትንሣኤ ልጆችም ስለሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ። ሙታን እንደሚነሡስ እግዚአብሔር፦ ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ’ ብሎ በቍጥቋጦው ዘንድ እንደ አነጋገረው ሙሴ ተናግሮአል። እንኪያስ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ሁሉም በእርሱ ዘንድ ሕያዋን ናቸውና።” ከጻፎችም ወገን የሆኑ ሰዎች፥ “መምህር ሆይ፥ መልካም ብለሃል” ብለው መለሱ። ከዚያ ወዲህ ግን ሊጠይቀው የደፈረ ማንም የለም። እንዲህም አላቸው፥ “ክርስቶስን እንዴት የዳዊት ልጅ ይሉታል? እርሱ ራሱ ዳዊት በመዝሙር መጽሐፍ ‘ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፥ ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስከ አደርጋቸው ድረስ’ ብሏል። እንግዲህ እርሱ ራሱ ዳዊት ‘ጌታዬ’ ያለው እንዴት ልጁ ይሆናል?” ሕዝቡም ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው። “ልብሳቸውን አንዘርፍፈው ወዲያ ወዲህ ማለትን ከሚሹ፥ በገበያ እጅ መነሣትንና በአደባባይ ፊት ለፊት፥ በማዕድም ጊዜ በከበሬታ መቀመጫ መቀመጥን ከሚወዱ ጻፎች ተጠበቁ። የመበለቶችን ገንዘብ የሚበሉ፥ ለምክንያት ጸሎትንም የሚያስረዝሙ እነዚህ ታላቅ ፍርድን ይቀበላሉ።”
የሉቃስ ወንጌል 20 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 20:20-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች