በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቈጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ ለሶርያ መስፍን በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመርያ ቈጠራ ሆነ። ሰው ሁሉ ሊቈጠር ወደየከተማው ሄደ። ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ቤተ ልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱ ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹም ወገን ነበርና። ፀንሳ ሳለች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ሄደ። በዚያ ሳሉም የምትወልድበት ቀን ደረሰ። የበኵር ልጅዋንም ወለደች፤ አውራ ጣቱንም አሰረችው፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በበረትም አስተኛችው፤ በማደርያቸው ቦታ አልነበራቸውምና። በዚያ ሀገር እረኞች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሀትንም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው። ለእናንተም ምልክቱ እንዲህ ነው፦ ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፥ በጨርቅም ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኛላቸሁ።” ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። “ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፥ ሰላምም በምድር፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” ይሉ ነበር። ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በዐረጉ ጊዜ እነዚያ እረኞች ሰዎች እርስ በርሳቸው፥ “እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ” አሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፤ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝቶ አገኙት። በአዩም ጊዜ የነገሩአቸው ስለዚህ ሕፃን እንደ ሆነ ዐውቀው አወሩ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ የነገሩአቸውን አደነቁ። ማርያም ግን ይህን ሁሉ ትጠብቀው፥ በልብዋም ታኖረው ነበር። እረኞችም እንደ ነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን በተፈጸመ ጊዜም ሕፃኑን ሊገዝሩት ወሰዱት፤ በማኅፀንዋ ሳትፀንሰው መልአኩ እንዳወጣለትም ስሙን ኢየሱስ አሉት። የመንጻታቸውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ እንደ ሙሴ ሕግ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሙት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። “በኵር ሆኖ የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይባላል” ተብሎ በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ታዘዘ ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ስለ እርሱ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡለት ዘንድ። በኢየሩሳሌምም ስሙ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ጻድቅና ደግ ሰው ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን ደስታቸውን ያይ ዘንድ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ነበር። የእግዚአብሔርንም መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። መንፈስም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደው፤ ዘመዶቹም በሕግ የተጻፈውን ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ጌታችን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ በአገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ በክንዱ ታቀፈው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው። እንዲህም አለ፤ “አቤቱ፥ እንደ አዘዝህ ዛሬ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ። ዐይኖች ትድግናህን አይተዋልና። በወገንህ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፥ ለአሕዛብ ብርሃንን፥ ለወገንህ ለእስራኤልም ክብርን ትገልጥ ዘንድ።” ዮሴፍና እናቱ ግን በእርሱ ላይ ስለሚናገረው ያደንቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው፤ ባንቺ ግን በልብሽ ፍላጻ ይገባል፤ የብዙዎቹን ዐሳብ ይገልጥ ዘንድ።” ከአሴር ወገን የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል ነቢይት ነበረች፤ አርጅታም ነበር፤ ከድንግልናዋም በኋላ ከባል ጋር ሰባት ዓመት ኖረች። ሰማንያ አራት ዓመትም መበለት ሆና ኖረች፤ በጾምና በጸሎትም እያገለገለች፥ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አትወጣም ነበር። ያንጊዜም ተነሥታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ድኅነት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለ እርሱ ተናገረች። በእግዚአብሔርም ሕግ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ጥበብንም የተመላ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረች።
የሉቃስ ወንጌል 2 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 2:1-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos