ዲዳና ደንቆሮ ጋኔንንም ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ዲዳና ደንቆሮ የነበረው ተናገረ፤ ሰዎችም አደነቁ። ነገር ግን ከመካከላቸው፥ “በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣቸዋል” ያሉ ነበሩ፤ እርሱም መልሶ፥ “ሰይጣን ሰይጣንን ማውጣት እንደምን ይቻለዋል?” አላቸው። ሌሎችም ሊፈትኑት ከእርሱ ዘንድ ከሰማይ ምልክትን ይፈልጉ ነበር። እርሱ ግን የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም እርስ በርሱ ቢለያይ ያ ቤት ይወድቃል። ሰይጣንስ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል ትላላችሁና። እኔ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆነ፥ ልጆቻችሁ በምን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ይፋረዱአችኋል። እኔ በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆነ እንግዲህ አሁን የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ኀይለኛ ሰው በጦር መሣሪያ ቤቱን የጠበቀ እንደ ሆነ ገንዘቡ ሁሉ ደኅና ይሆናል። ከእርሱ የሚበረታው ቢመጣና ቢያሸንፈው ግን፥ ይታመንበት የነበረውን የጦር መሣሪያውን ይገፈዋል፤ የማረከውንና የዘረፈውን ገንዘቡንም ይወስዳል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ባለጋራዬ ነው፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ይበትንብኛል። “ክፉ ጋኔንም ከሰው በወጣ ጊዜ ውኃ ወደሌለበት ምድረ በዳ ይሄዳል፤ የሚያርፍበትንም መኖሪያ ይሻል፤ ያላገኘ እንደ ሆነም ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል። በመጣም ጊዜ ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል። ከዚህም በኋላ ይሄድና ከእርሱ የሚከፉ ሌሎች ባልንጀሮቹን ሰባት አጋንንት ያመጣል፤ ገብተውም በዚያ ሰው ያድሩበታል፤ ለዚያ ሰውም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው የከፋ ይሆንበታል።” ከዚህም በኋላ ይህን ሲናገር ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን አሰምታ፥ “የተሸከመችህ ማኅፀን ብፅዕት ናት፤ የጠባሃቸው ጡቶችም ብፁዓት ናቸው” አለችው። እርሱም፥ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁ ናቸው” አላት። ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው ሳሉ እንዲህ ይላቸው ጀመረ ፥ “ይቺ ትውልድ ክፉ ናት፤ ምልክትም ትሻለች፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጣትም። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው የሰው ልጅም ለዚች ትውልድ እንዲሁ ምልክት ይሆናታል። የአዜብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚች ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፋረዳቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ልትሰማ ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚች ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፋረዱአታል፤ ያሳፍሩአታልም፤ ዮናስ በሰበከላቸው ጊዜ ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፥ ከዮናስ የሚበልጥ በዚህ አለ።
የሉቃስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 11:14-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች