ኦሪት ዘሌዋውያን 8
8
ስለ አሮንና ስለ ልጆቹ ቅብዐተ ክህነት
(ዘፀ. 29፥1-37)
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዐቱንም ዘይት፥ ለኀጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ መሶብ ውሰድ፤ 3ማኅበሩንም ሁሉ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው።” 4ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩንም ሁሉ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ሰበሰበ። 5ሙሴም ማኅበሩን፥ “እግዚአብሔር ታደርጉ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው።
6ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፤ በውኃም አጠባቸው። 7እጀ ጠባብም አለበሰው፤ በመታጠቂያም አስታጠቀው፤ የበፍታ ቀሚስም አለበሰው፤ ልብሰ መትከፍም ደረበለት፤ በልብሰ መትከፉም አሠራር ላይ በብልሃት በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። 8ልብሰ እንግድዓውንም በእርሱ ላይ አደረገ፤ በልብሰ እንግድዓውም ላይ የምልክትና የእውነት መገለጫዎችን#ዕብ. “ኡሪምና ቱሚም” ይላል። አኖረበት። 9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ አክሊል አደረገለት፤ በአክሊሉም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን የወርቅ መርገፍ አደረገ።
10ሙሴም የቅብዐቱን ዘይት ወሰደ፤ ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ 11ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ፤ ድንኳኒቱንና ዕቃዋን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 12ከቅብዐቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ ቀባው፤ ቀደሰውም። 13እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፤ የበፍታ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፤ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፤ አክሊልም ደፋላቸው።
14የኀጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኀጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15አረዱትም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፤ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው። 16ሙሴም በሆድ ዕቃው ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጉበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ ስባቸውንም ወሰደ፤ በመሠዊያውም ላይ ጨመረው። 17እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቍርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ።
18ሙሴም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19ሙሴም ያን በግ አረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን፥ ብልቶቹንም፥ ስቡንም ጨመረ። 21የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ ጨመረ፤ ይህ በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ።
22ሙሴም ለቅድስና የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ፤ 23አረዱትም። ሙሴም ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ቀባው። 24የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ ቀባ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጉበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26በእግዚአብሔር ፊት ካለው የቅድስና መሶብ አንድ የቂጣ እንጎቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቍርባንን አቀረበ፤ 28ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አኖረው። በጎ መዓዛ የቅድስና መሥዋዕት ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 29ሙሴም ከቅድስናው አውራ በግ ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበው ዘንድ ቈራረጠ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ።
30ሙሴም ከቅብዐቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ከአለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም፥ የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ።
31ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው፥ “ሥጋውን በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በተቀደሰው ቦታ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይብሉት ብሎ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ በዚያ እርሱንና በቅድስናው መሶብ ያለውን እንጀራ ብሉ። 32ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት አቃጥሉት። 33ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ። 35እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ የእግዚአብሔርንም ሥርዐት ጠብቁ፤” 36አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ