ኦሪት ዘሌዋውያን 21
21
ስለ ካህናት ቅድስና
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፥ “ከወገናቸው በሞተ ሰው ራሳቸውን እንዳያረክሱ ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ንገራቸው። 2ከቅርብ ዘመዶቻቸው፥ ከአባቶቻቸው፥ ወይም ከእናቶቻቸው፥ ወይም ከወንዶች ልጆቻቸው፥ ወይም ከሴቶች ልጆቻቸው፥ ወይም ከወንድሞቻቸው፥ 3ወይም ከቀረበች ያላገባች ድንግል እኅት በቀር ራሳቸውን አያርክሱ። 4ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ ከሕዝቡ በማንም አይርከስ።#ዕብ. “የሕዝቡ አለቃ ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ አይርከስ” ይላል። 5ስለ ሞተው ሰው ራሳቸውን አይላጩ፤ ጢማቸውንም አይላጩ፤ ሥጋቸውንም አይንጩ። 6ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፤ የአምላካቸውንም ስም አያርክሱ፤ የእግዚአብሔርን#ዕብ. “የእሳት ቍርባን” ይላል። መሥዋዕትና የአምላካቸውን መባ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ። 7ለአምላኩ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፋታችውን አያግባ። 8የአምላክህን መባ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ። 9የካህንም ሰው ልጅ በግልሙትና ራስዋን ብታረክስ በግልሙትና አባቷን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል።
10“በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ፥ ከወንድሞቹ የተለየው ካህን ራሱን አይላጭ፤ ልብሱንም አይቅደድ። 11ወደ ሞተ ሰው ሁሉ አይግባ፤ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ። 12የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፤ የአምላኩንም ቅዱስ ስም አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13እርሱም ከወገኑ ድንግል ሴትን ያግባ። 14ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ የተጠላችውን ወይም ጋለሞታዪቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከወገኑ ድንግሊቱን ያግባ፤ 15እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል።”
16እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 17“ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ከወገንህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን መባ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። 18ንጹሕ ያልሆነ ሰው ሁሉ አይቅረብ፤ ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም ጆሮ ቈራጣ፥ 19ወይም እጀ ሰባራ፥ ወይም እግረ ሰባራ፥ 20ወይም ጎባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዐይነ መጭማጫ፥ ወይም ቅንድበ መላጣ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም የአባለዘሩ ፍሬ አንድ የሆነ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። 21ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን መባ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። 22የቅዱሱንና የቅዱሰ ቅዱሳኑን የአምላኩን መባ ይብላ፤ 23ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶችን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፤ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” 24ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገራቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 21: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ