ኦሪት ዘሌዋውያን 2
2
የእህል ቍርባን
1“ማናቸውም ሰው ቍርባን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲሆን ቢያቀርብ፥ ቍርባኑ ከመልካም ስንዴ ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስስበታል፤ ነጭ ዕጣንም ይጨምርበታል፤ ይህም መሥዋዕት ነው። 2ወደ ካህኑ ወደ አሮን ልጆች ያመጣዋል፤ ከመልካም ስንዴ ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ነጩንም ዕጣን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 3ከመሥዋዕቱም የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር መሥዋዕት የተረፈ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው።
4“በእቶን የተጋገረውን ቍርባን ስታቀርብ፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ስንዴ ዱቄት፥ የቂጣ እንጎቻ ወይም በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን። 5ቍርባንህም በምጣድ የተጋገረ ቍርባን ቢሆን፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ስንዴ ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6ቈርሰህም ዘይት ታፈስስበታለህ፤ የእግዚአብሔር መሥዋዕት ነው። 7ቍርባንህም በመቀቀያ የበሰለ ቍርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ስንዴ ዱቄት የተደረገ ይሁን። 8ከዚህም ያደረግኸውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ታመጣለህ፤ ወደ ካህኑም ታቀርበዋለህ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል። 9ካህኑም ከቍርባኑ መታሰቢያውን ይወስዳል፤ በመሠዊያውም ላይ ይጨምረዋል። ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው የሚቃጠል ቍርባን ነው። 10ከመሥዋዕቱም የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር መሥዋዕት የተረፈ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው።
11“ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት፤ እርሾ ያለበት ነገር፥ ማርም ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡምና። 12እነዚህንም ዐሥራት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ለበጎ መዓዛ በመሠዊያው ላይ አይቀርቡም። 13የምታቀርቡት ቍርባን ሁሉ በጨው ይጣፈጣል፤ የአምላክህም ቃል ኪዳን ጨው ከቍርባንህ አይጕደል፤ በቍርባናችሁ ሁሉ ላይ ጨው ትጨምራላችሁ።
14“ከመጀመሪያው እህልህ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ብታቀርብ በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸት ታቀርባለህ። 15ዘይትም ታፈስስበታለህ፤ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። 16ካህኑም ከተፈተገው እህል፥ ከዘይቱም ወስዶ ከዕጣኑ ጋር መታሰቢያውን ያቀርባል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ