አሌፍ። በቍጣው በትር ችግር ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ የመከራውንም ጎዳና በእኔ ላይ አቀና። እንደ ቀድሞ ሙታን በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴንም አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ተከለከለ። መንገዴን በዓለት ላይ ሠራ፤ ጎዳናዬንም አጠረ። ዳሌጥ። እንደምትሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። ተከተለኝ፤ ጨረሰኝ፤ ባድማም አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻውም እንደ ዒላማ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ መሳቂያ ሆንሁ፤ ቀኑንም ሁሉ ዘፈኑብኝ። ምሬትን አጠገበኝ፤ በሐሞትም አሰከረኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፤ አመድም አቃመኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቀ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኀይሌን፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለውን ተስፋዬን አጣሁ። ዛይ። ስደቴንና ችግሬን፥ እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፤ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፥ “እግዚአብሔር እድል ፋንታዬ ነው፤ ስለዚህ ጠበቅሁት” አለች። ጤት። እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው፤ ለምትሻውና ለምትታገሥ፥ ዝም ብላም የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ለምታደርግ ነፍስ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ ይሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጕንጩን ለሚመታው ይሰጣል፤ ስድብንም ይጠግባል። ካፍ። ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፤ ያሳዘነውን ሰው እንደ ይቅርታው ብዛት ይምረዋልና፤ ከልቡ አልተቈጣምና፥ የሰውንም ልጆች አላሳዘነምና፥ ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ በሚፈርድበት ጊዜ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ እግዚአብሔር አላዘዘም።
ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 3:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች