መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 23
23
የኢያሱ መሰናበቻ ንግግር
1እንዲህም ሆነ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፈ በኋላ፥ ኢያሱ ሸመገለ፤ ዘመኑም ዐለፈ፤ 2ኢያሱ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውንም፥ አለቆቻቸውንም፥ ፈራጆቻቸውንም፥ ሹሞቻቸውንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ እነሆ ሸምግያለሁ፤ ዘመኔም አልፎአል፤ 3እናንተም አምላካችን እግዚአብሔር በፊታችሁ ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ስለ እናንተ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነው። 4እነሆ እኔ ካጠፋኋቸው አሕዛብ ሁሉ ጋር ከዮርዳኖስ ጀምሮ በፀሐይ መግቢያ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ለነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆኑ የቀሩትን እነዚህን አሕዛብ በዕጣ ከፈልሁላችሁ። 5አምላካችሁም እግዚአብሔር እርሱ ከፊታችሁ እስኪደመሰሱ ድረስ ያጠፋላችኋል፤ ከፊታችሁም እነርሱንና ንጉሦቻቸውን እስኪያጠፋቸው ድረስ የዱር አራዊትን ይሰድድባቸዋል፤#“ከፊታችሁም እነርሱንና ንጉሦቻቸውን እስኪያጠፋቸው ድረስ የዱር አራዊትን ይሰድድባቸዋል” የሚለው ከግሪክ ሰባ. ሊ. የተገኘ ነው። አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ። 6በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ትጠብቁና ታደርጉ ዘንድ በጣም በርቱ፥#ግእዙ “ከመ ኢተአብሱ” የሚል ይጨምራል። ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። 7በእናንተም መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውም ስሞች በእናንተ መካከል አይጠሩ፤ አትማሉባቸውም፤ አታምልኳቸውም፤ አትስገዱላቸውም፤ 8ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት አምላካችሁ እግዚአብሔርን ተከተሉ። 9እርሱ እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኀይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ ያጠፋቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ የተቋቋማችሁ በፊታችሁ ማንም የለም። 10አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ነገረን ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። 11አምላካችን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ። 12እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ፥ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥ 13አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በእግራችሁም ችንካር፥ በዐይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያጠፋቸው ራሳችሁ ዕወቁ።
14“እኔም በምድር እንዳሉት ሰዎች ሁሉ ዛሬ ወደ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም አምላካችን እግዚአብሔር ስለ እኛ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ፥ በነፍሳችሁም ሁሉ ዕወቁ፤ ሁሉ ደርሶናል፤ ከእርሱም ያላገኘነው የለም። 15አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። 16አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ብታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።”#“በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል ... ትጠፋላችሁ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 23: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ