መጽሐፈ ኢዮብ 15
15
የኤልፋዝ ሁለተኛ ንግግር
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ነፋስ በሆነ ዕውቀት ይመልሳልን?
ሆዱንስ በሥቃይ ይሞላልን?#ግእዝ “ወአጽገብከ ጻዕረ ለከርሥነ” ይላል።
3ከከንቱ ነገር፥
ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን?
4አንተ እግዚአብሔርን መፍራት ትተሃልን?
በእግዚአብሔርስ ፊት እንዲህ ያለውን ቃል ትናገራለህን?
5ከአፍህ ንግግር የተነሣ መጠንህ ይታወቃል፥
የኀያላኑንም ቃል አልለየህም።
6የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤
ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል።
7በውኑ ከሰው ቀድመህ የተፈጠርህ ሰው አንተ ነህን?
# ግእዙ “ወይስ እንደ ውርጭ ረግተሃልን” ይላል። ወይስ ከተራሮች በፊት ተፀነስህን?
8የእግዚአብሔርንስ ትእዛዝ#ዕብ. “ምሥጢር” ይላል። ሰምተሃልን?
ወይስ እግዚአብሔር አማካሪው አድርጎሃልን?
ወይስ ጥበብን ለብቻህ አድርገሃልን?
9እኛ የማናውቀውን አንተ ምን ታውቃለህ?
እኛስ የማናስተውለውን አንተ ምን ታስተውላለህ?
10በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ፥
ሽበትም ያላቸው ሽማግሎች ከእኛ ጋር አሉ።
11ጥቂት ብትበድል ተገረፍህ፥
ይህም የተናገርኸው ነገር በዐቅምህ አይደለም።
12“ልብህስ ለምን ይደፍራል?
ዐይኖችህስ ለምን ይገላምጣሉ?
13በእግዚአብሔር ፊት በቍጣ ትመልስ ዘንድ፤
እንደዚህስ ያለ ነገር ከአፍህ ታወጣ ዘንድ፤
14ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሟች ሰው ማን ነው?
ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ማን ነው?
15እነሆ፥ በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤
ሰማይም በፊቱ ንጹሕ አይደለም።
16ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥
ኀጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?
17“ስማኝ ልንገርህ፥
እነሆም ያየሁትን እነግርሃለሁ፤
18ጠቢባን የተናገሩትን፥
አባቶቻቸውም ያልሰወሩትን እነግርሃለሁ።
19ምድር ለእነርሱ ብቻ ተሰጥታለችና፤
በመካከላቸውም እንግዳ ሕዝብ አልገባባቸውምና።
20የኃጥእ ሰው ዕድሜው በጭንቅ ያልፋል፥
ለግፈኛ የተመደቡ ዓመታቱም ሁሉ የተቈጠሩ ናቸው።
21የሚያስደነግጥ ድምፅም በጆሮው ነው፤
በደኅንነትም ይኖር ዘንድ ተስፋ በሚያደርግበት ጊዜ ጥፋት ይመጣበታል።
22ከጨለማ ተመልሶ እንዲወጣ ተስፋ የለውም፥
ለሰይፍም ኀይል ፈጽሞ ተዳርጎአል።
23ለአሞራዎችም ምግብ ሆኖ ተሰጥቶአል
በድን ሆኖ እንደሚቈይም እርሱ ራሱ ያውቃል።
የጨለማ ቀንም እንደ አውሎ ነፋስ ትወስደዋለች።
24መከራና ጭንቀት ይመጡበታል፤
በፊት እንደ ተሰለፈ መኰንን ይወድቃል።
25እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥
ሁሉን በሚችል አምላክ ፊትም አንገቱን አደንድኖአልና።
26በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ በጋሻው ጕብጕብ፥
ከውርደት ጋር እየሰገገ ይመጣበታልና።
27በስብም ፊቱን ከድኖአልና
ስቡንም በወገቡ ላይ አድርጎአልና፥
28በተፈቱም ከተሞች ውስጥ ይኖራል፥
ሰውም በሌለባቸው ቤቶች ይገባል፥
እርሱ ያዘጋጀውንም ሌሎች ይወስዱታል።
29“እርሱ ባለጠጋ አይሆንም፤ ሀብቱም አይጸናም፤
ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፤
30ከጨለማ በምንም አያመልጥም፤
ነፋስም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥
አበባዎቹም ይረግፋሉ።
31ለመኖር ተስፋ አያደርግም፤
ፍጻሜው ከንቱ ይሆናልና።
32ቀኑ ሳይደርስ መከሩ ይጠፋል፥
ቅርንጫፉም አይለመልምም።
33ጮርቃውም ይረግፋል፤
እንደ ወይራም አበባ ይወድቃል።
34ለኃጥኣን ሁሉ ሞት ምስክራቸው ነው፥
እሳት የጉቦ ተቀባዮችን ቤት ይበላል።
35በሆዳቸው ጭንቅትን ይፀንሳሉ፥
ከንቱ ነገርንም ይወልዳሉ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. በነጠላ።
ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 15: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ