ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው፥ “መምህር ሆይ፥ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም፥ “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና። ስለዚህም ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል ስለ አልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳልና፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የሚወለድ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ኒቆዲሞስም መልሶ፥ “ይህ ሊሆን እንዴት ይቻላል?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን እንዴት ይህን አታውቅም?” አለው። እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም። በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው። ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና።
የዮሐንስ ወንጌል 3 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 3:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች