ትንቢተ ኤርምያስ 49
49
በአሞን ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ
1ስለ አሞን ልጆች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሚልኮም ጋድን ይወርስ ዘንድ ሕዝቡም በከተሞቹ ላይ ይቀመጥ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች የሉትምን? ወይስ ወራሽ የለውምን? 2ስለዚህ እነሆ በአሞን ልጆች ከተማ በራባት ላይ የሰልፍ ውካታን የማሰማበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለጥፋትም ትሆናለች፥ መንደሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ እስራኤልም የወረሱትን ይወርሳል፥ ይላል እግዚአብሔር። 3ሐሴቦን ሆይ! ጋይ#“ጋይ” የሚለው በግእዝ የለም። ፈርሳለችና አልቅሽላት፤ እናንተም የራባት ሴቶች ልጆች ሆይ! ሚልኮም፥ ካህናቱና አለቆቹም በአንድነት ይማረካሉና ጩኹ፤ ማቅም ታጠቁ፤ አልቅሱም። 4ማን ይመጣብኛል ብለሽ በሀብትሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! በጠፉ ሸለቆዎችሽ ስለ ምን ትመኪያለሽ? 5እነሆ በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ ፍርሀትን አመጣብሻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትሰደዳላችሁ፤ የሚሸሹትንም የሚሰበስብ የለም። 6ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአሞንን ልጆች ምርኮ እመልሳለሁ ይላል እግዚአብሔር።”#ምዕ. 49 ከቍ. 1 እስከ 6 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 30 ከቍ. 1 እስከ 15 ነው።
7ስለ ኤዶምያስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በውኑ በቴማን ጥበብ የለምን? ከብልሃተኞችስ ምክር ጠፍቶአልን? ጥበባቸውስ አልቆአልን? 8እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ! የዔሳውን ጥፋት፥#“የዔሳውን ጥፋት” የሚለው በዕብ. በቻ። የምጐበኝበትን ጊዜ አመጣበታለሁና ሽሹ፤ ወደ ኋላም ተመለሱ፤ በጥልቅም ጕድጓድ ውስጥ ተቀመጡ። 9ወይን ለቃሚዎች ቢመጡብህ፥ ቃርሚያውን አይተዉልህምን? ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በእጃቸው” የሚል አለው። የሚያጠፉት እስኪበቃቸው ድረስ አይደለምን? 10እኔ ግን ዔሳውን አራቆትሁት፤ የተሸሸጉትንም ስፍራዎች ገለጥሁ፤ ይሸሸግም ዘንድ አይችልም፤ ዘሩም፤ ወንድሞቹም፤ ጎረቤቶቹም ጠፍተዋል፥ እርሱም የለም። 11ድሃአደጎችህን ተው፤ እኔም በሕይወት አኖራቸዋለሁ፤ መበለቶችህም በእኔ ይታመናሉ። 12እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ ጽዋውን ያልተገባቸው ሰዎች ጠጥተውታል፤ አንተም መንጻትን ትነጻለህን? እንግዲህ አትነጻም መጠጣትን ትጠጣለህና። 13ባሶራ ምድረ በዳ፥ መሰደቢያና መረገሚያም እንድትሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከተሞችዋም ሁሉ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ።
14“ከእግዚአብሔር ዘንድ መስማትን ሰምቻለሁ፤ በአሕዛብ ሀገሮች ተሰብሰቡ፤ በእርስዋም ላይ ኑ፤ እርስዋንም ውጓት፥ የሚል መልእክተኛ ተልኳል። 15እነሆ በሕዝብ ዘንድ የተጠቃህ፥ በሰዎችም ዘንድ የተናቅህ አድርጌሃለሁ። 16በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትቀመጥ፥ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ! ድፍረትህና የልብህ ኵራት አነሣሥተውሃል። ቤትህንም ምንም እንደ ንስር ከፍ ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር።
17“ኤዶምያስም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ የሚያልፍባትም ሁሉ ይደነቃል፤ ስለ መጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። 18ሰዶምና ገሞራ፥ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ከተሞች እንደ ተገለበጡ፥ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤ እንዲሁ በዚያ ሰው አይቀመጥም፤ የሰው ልጅም አይኖርባትም። 19እነሆ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና ከዮርዳኖስ ዳር ወደ ኤታም እንደ አንበሳ ይወጣል፤ ጐልማሶችንም#ዕብ. “የተመረጠውንም” ይላል። በእርስዋ ላይ እሾማለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜን የሚወስን#“ጊዜ የሚወስን” የሚለው በዕብ. ብቻ። ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው?” 20ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ስዎች ላይ ያሰባትን ዐሳብ ስሙ፤ ትንንሾች በጎችን ዘርፈው ይወስዷቸዋል፤ የሚኖሩባትንም ማደሪያቸውን ባድማ ያደርጉባቸዋል። 21ከመውደቃቸው ድምፅ የተነሣ ምድር ደነገጠች፤ ድምፅዋም እንደ ባሕር ድምፅ እነሆ ተሰማ። 22እነሆ እንደ ንስር ወጥቶ ይመለከታል፤#ዕብ. “ይበርራል” ይላል። ክንፉንም በባሶራ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በምሽጎችዋ” ይላል። ላይ ይዘረጋል፤ በዚያም ቀን የኤዶምያስ ኀያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል።#ምዕ. 49 ከቍ. 7 እስከ 22 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 29 ከቍ. 7 እስከ 22 ነው።
23“ስለ ደማስቆ፤ ክፉ ወሬ ሰምተዋልና ሐማትና አርፋድ አፈሩ፤ ቀለጡም፤ እንደ ባሕርም ተነዋወጡ፤ ያርፉም ዘንድ አይችሉም። 24ደማስቆ ደከመች፤ ተሸብራም ሸሸች፤ እንቅጥቅጥም ያዛት፤ እንደ ወላድም ሴት ጣርና ምጥ ያዛት። 25የወደዱትን ቦታና ከተማ እንዴት አልተዉላትም? 26ስለዚህ ጐበዛዝቷ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፤ በዚያም ቀን ሰልፈኞች ሁሉ ይወድቃሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 27በደማስቆም ቅጥር ላይ እሳት አነድዳለሁ፤ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች።”#ምዕ. 49 ከቍ. 23 እስከ 27 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 30 ከቍ. 23 እስከ 27 ነው።
28የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታቸው ስለ ቄዳርና ስለ አሦር መንግሥታት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ተነሡ ወደ ቄዳርም ውጡ፤ የምሥራቅንም ልጆች አጥፉ። 29ድንኳናቸውንና በጎቻቸውን#ዕብ. “መንጋቸውን” ይላል ይወስዳሉ፤ መጋረጃዎቻቸውንና ዕቃቸውን ሁሉ፥ ግመሎቻቸውንም ለራሳቸው ይወስዳሉ፤ በዙሪያቸውም ሁሉ ጥፋትን ጥሩባቸው። 30እናንተ በአሦር የምትኖሩ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ተማክሮባችኋልና፥ ክፉ አሳብንም አስቦባችኋልና ሽሹ፤ ወደ ሩቅም ሂዱ፤ በጥልቅ ጕድጓድም ውስጥ ተቀመጡ፥” ይላል እግዚአብሔር። 31“ተነሡ፤ ዕረፍት ወዳለበት፥ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው፥ ደጅና መዝጊያ፥ መወርወሪያም ወደሌለው፥ ብቻውንም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ዝመቱ። 32ግመሎቻቸው ለምርኮ ይሆናሉ፤ የእንስሶቻቸውም ብዛት ለጥፋት ይሆናል፤ ጠጕራቸውንም በዙሪያ የሚላጩትን ሰዎች ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከዳርቻቸው ሁሉ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር፥ 33አሦርም የወፎች መኖሪያና የዘለዓለም ባድማ ትሆናለች፤ በዚያም ሰው አይኖርም፤ የሰው ልጅም አይቀመጥባትም።
በኤላም ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ
34በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በመጀመሪያው ዓመተ መንግሥት ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 35“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ዋና የኀይላቸው መሣሪያ የሆነውን የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ። 36ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፤ ወደ እነዚያም ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች የማይደርሱበት ሕዝብ አይገኝም። 37በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን በሚሹአት ፊት ኤላምን አስደነግጣለሁ። ክፉ ነገርን እርሱም ጽኑ ቍጣዬን አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በኋላቸው ሰይፍን እሰድድባቸዋለሁ። 38ዙፋኔንም በኤላም አኖራለሁ፤ ከዚያም ንጉሡንና መሳፍንቱን አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 39ነገር ግን በኋለኛው ዘመን እንዲህ ይሆናል፤ የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር።#ምዕ. 49 ከቍ. 28 እስከ 33 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 30 ከቍ. 23 እስከ 33 ነው ምዕ. 49 ከቍ. 34 እስከ 38 በግሪክ ሰባ. ሊ ምዕ. 25 ከቍ. 14 እስከ 20 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 49: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ