ትንቢተ ኤርምያስ 30
30
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ተስፋ
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። እንዲህም አለው፤ 2“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ። 3እነሆ! የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይገዙአታል።”
4እግዚአብሔር በእስራኤልና በይሁዳ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 5እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “የሚያስፈራ ድምፅ ትሰማላችሁ፤ ፍርሀት ነው እንጂ ሰላም አይደለም። 6ጠይቁ፤ ወንድ ይወልድ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ ስለ ምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ፥ ፊቱም ሁሉ ወደ ጥቍረት ተለውጦ አየሁ? 7ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፤ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል። 8በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፤ እስራትህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለሌላ አትገዛም። 9ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም፥ ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ።
10“እነሆ አንተን ከሩቅ፥ ዘርህንም ከምርኮ ሀገር አድናለሁና ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ ያዕቆብም ይመለሳል፤ ያርፍማል፤ ተዘልሎም ይቀመጣል፤ ማንም አያስፈራውም። 11አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥” ያለ ቅጣትም ከቶ አልተውህም።”#ምዕ. 30 ቍ. 10 እና 11 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስብራትህ የማይፈወስ፥ ቍስልህም ክፉ ነው። 13ትጠገን ዘንድ ክርክርህን የሚፈርድልህ ሰው የለም፤ ቍስልህንም የሚፈውስ መድኀኒት የለህም። 14ወዳጆችህ ሁሉ ረስተውሃል፤ አይፈልጉህምም፤ በደልህ ታላቅ ስለ ሆነ፥ ኀጢአትህም ስለ በዛ፥ በጠላት ማቍሰልና በጨካኝ ቅጣት አቍስዬሃለሁና። 15ቍስልህ የማይፈወስ ሆኖአልና ስለ ስብራትህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ ስለ ሆነ፥ ኀጢአትህም ስለ በዛ፥ ይህን አድርጌብሃለሁ። 16ስለዚህ የሚበሉህ ሁሉ ይበላሉ፤ የሚማርኩህም ሁላቸው ይማረካሉ፤ የዘረፉህም ይዘረፋሉ፤ የሚማርኩህንም ሁሉ ለመማረክ አሳልፌ እሰጣለሁ።#ምዕ. 30 ቁ. 15 እና 16 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም ተዘዋውሮአል። 17እኔ ከክፉ ቍስልሽ እፈውስሻለሁ፤ ጤናሽን እመልስልሻለሁ፤ ቍስልሽንም እፈውሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማንም የማይሻት፥ የተጣለች ጽዮን ብለው ጠርተውሻልና።”
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱም በጕብታዋ ላይ ትሠራለች፤ አዳራሹም እንደ ዱሮው የሰው መኖሪያ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሕዝቡም እንደየሥርዐታቸው ይመለሳሉ” ይላል። ይሆናል። 19ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፈን ድምፅ ይወጣል፤ እኔም አበዛቸዋለሁ፤ አያንሱምም። 20ልጆቻቸውም እንደ ቀድሞው ይሆናሉ፤ ምስክርነታቸውም#ዕብ. “ማኅበራቸውም” ይላል። በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፤ የሚያስጨንቁአቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ። 21አለቃቸውም ከእነርሱ ውስጥ ይሾማል፤ ገዢአቸውም ከመካከላቸው ይወጣል፤ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ እኔም እመልሳቸዋለሁ፤ ወደ እኔ ይመለስ ዘንድ ልብ የሰጠው ማን ነው? ይላል እግዚአብሔር። 22እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።”#ምዕ. 30 ቍ. 22 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
23እነሆ የእግዚአብሔር ቍጣ ለመቅሠፍት ወጥቶአል፤ የመዓቱንም ጥፋት በኃጥኣን ራስ ላይ አምጥቶአል፤ 24የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛውም ዘመን ታውቁታላችሁ።#ምዕ. 30 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 37 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 30: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ