ትንቢተ ኤርምያስ 26
26
ኤርምያስ ለፍርድ እንደ ቀረበ
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣ፤ አለም፦ 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ቁም፤ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ይሰግዱ ዘንድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ ትነግራቸው ዘንድ ያዘዝሁህን ቃል ሁሉ ተናገራቸው፤ አንዲትም ቃል አታጕድል። 3ምናልባት እያንዳንዳቸው ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ።” 4እንዲህም በላቸው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ትሄዱ ዘንድ ባትሰሙኝ፥ 5የባሪያዎችን የነቢያትን ቃል ትሰሙ ዘንድ በማለዳ ወደ እናንተ ብልካቸው አልሰማችሁም። 6ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፤ ይችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ ርግማን አደርጋታለሁ።”
7ካህናቱም፥ ነቢያተ ሐሰትም፥ ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በእግዚአብሔር ቤት ይህን ቃል ሲናገር ሰሙ። 8ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ በፈጸመ ጊዜ ካህናትና ነቢያተ ሐሰት፥ ሕዝቡም ሁሉ፥ “ሞትን ትሞታለህ” ብለው ያዙት። 9በእግዚአብሔር ስም፥ “ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይችም ከተማ ባድማ ትሆናለች፤ የሚኖርባትም የለም ብለህ ስለ ምን ትንቢት ተናገርህ?” ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰብስበው ነበር።
10የይሁዳም አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ ከንጉሡ ቤት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በአዲሱም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ። 11ካህናቱና ነቢያተ ሐሰትም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ፥ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁ በዚች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሮአልና ይህ ሰው ሞት የሚገባው ነው” ብለው ተናገሩ። 12ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “በሰማችሁት ቃል ሁሉ፥ በዚች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እናገር ዘንድ እግዚአብሔር ልኮኛል። 13አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፤ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። 14እኔ ግን፥ እነሆ በእጃችሁ ነኝ፤ በዐይናችሁ መልካምና ቅን የመሰለውን አድርጉብኝ። 15ነገር ግን ይህን ቃል ሁሉ በጆሮአችሁ እናገር ዘንድ በእውነቱ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛልና ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚች ከተማ፥ በሚኖሩባትም ላይ እንድታመጡ በርግጥ ዕወቁ።”
16አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያተ ሐሰት፥ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮናልና ሞት አይገባውም” አሉ። 17ከሀገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ አሏቸው። 18“ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት ይናገር ነበር፤ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል ብሎ ተናገረ። 19በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተዉምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።”
20ደግሞም በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም የቂርያትይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኡርያ ይባል ነበር፤ በዚችም ከተማ፥ በዚችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገረ። 21ንጉሡም ኢዮአቄም፥ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኡርያም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ፤ ወደ ግብፅም ገባ። 22ንጉሡም ኢዮአቄም ሰዎችን ወደ ግብፅ ላከ፤ የአክቦርን ልጅ ኤልናታንን፥ ሌሎችንም ሰዎች ከርሱ ጋራ ወደ ግብፅ ላካቸው።#“የአክቦርን ልጅ ኤልናታንን፥ ሌሎችንም ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ ላካቸው” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 23ከግብፅም ኡርያን አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው፤ ሬሳውንም በሕዝብ መቃብር ጣለው። 24ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።#ምዕ. 26 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 33 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 26: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ