መጽሐፈ መሳፍንት 5
5
የዲቦራና የባርቅ መዝሙር
1በዚያችም ቀን ዲቦራና የአቢኒሔም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ዘመሩ፦#ግእዙ “ዲቦራ በባርቅ ፊት ዘመረች” ይላል።
2በእስራኤል ውስጥ መሳፍንት ስለ መሩ
ሕዝቡም ስለ ፈቀዱ፥
እግዚአብሔርን አመስግኑት።
3ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤
ጽኑዓን መኳንንትም ሆይ፥ አድምጡ፤
እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤
እኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።
4አቤቱ! ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥
ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥
ምድሪቱ ተናወጠች፤ ሰማያትም ጠልን አንጠባጠቡ፤
ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠባጠቡ።
5ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ተነዋወጡ፤
ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ፤
6በሐናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥
በኢያዔል ዘመን ነገሥት መንገዶችን ተዉ፤
በስርጥ መንገድም ይሄዱ ነበር፤
በጠማማ መንገድም ሄዱ።
7መተርጕማን ከእስራኤል ዘንድ አለቁ፥
ዲቦራ እስክትነሣ ድረስ፥
ለእስራኤልም እናት ሆና እስክትነሣ ድረስ አለቁ።
8አዲሶች አማልክትን መረጡ፤
በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤
በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታዩም።
9ልቤ ለእስራኤል ወደ ታዘዘው ትእዛዝ ነው፤
እናንተ የእስራኤል ኀያላን፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በሕዝቡ መካከል ፈቃደኞች የሆናችሁ” ይላል።
እግዚአብሔርን አመስግኑት።
10በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በቀትር ጊዜ በእንስት አህያ ላይ የምትጫኑ” ይላል።
በፍርድ ወንበር ላይየምትቀመጡ፥
በመንገድም የምትሄዱ በቃላችሁ ተናገሩ።
11በብዙዎች ደስተኞች መካከል መሰንቆን ምቱ፤
በዚያ ለእግዚአብሔር የጽድቅ ሥራን፥
በእስራኤልም ውስጥ ጽድቅንና ኀይልን ያቀርባሉ።
ያንጊዜም የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ከተማዎቹ ወረዱ።#ምዕ. 5 ቍ. 11 ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. ከግእዙ ልዩ ነው።
12ተነሺ፥ ዲቦራ ሆይ፦ ተነሺ፤
አእላፍን ከሕዝብ ጋር አስነሺ፤
ተነሺ፤ ተነሺ፤ ቅኔውንም ተቀኚ፤
ባርቅ ሆይ! በኀይል ተነሣ፤
ዲቦራም ባርቅን አጽኚው፥
የአቢኒሔም ልጅ ባርቅም ሆይ! ምርኮህን ማርክ።
13በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኀያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤
እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኀያላን ላይ ወረደ።
14በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥
ብንያም ሆይ! በሕዝብ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤
አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።
15የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤
ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤
ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኮሉ፤
በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።
16መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት፥
በበጎች ጉረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ?
በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።
17ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤
ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ?
አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥
በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።
18ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፤
ንፍታሌምም በሀገሩ ኮረብታ ላይ ነው።
19ነገሥታት መጡ፤ ተዋጉም፤
በዚያ ጊዜ በመጌዶ ውኆች አጠገብ በቶናሕ
የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤
በቅሚያም ብርን አልወሰዱም።
20ከዋክብት በሰማይ ተዋጉ፤
በሰልፋቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።
21ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥
የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በርቺ።
22ያን ጊዜ ከኀያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ፥
የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።
23የእግዚአብሔር መልአክ አለ፥ “ሜሮዝን ርገሙ፤ ወደ እግዚአብሔር ርዳታ አልመጡምና፥
በኀያላን መካከል ወደ እርሱ ርዳታ አልመጡምና፥
በቤቶችዋ ያሉትን ሰዎች ፈጽማችሁ ርገሙ።”
24የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል፥
ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤
በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።
25ውኃ ለመነ፤ ወተትም ሰጠችው፤
በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት።
26ግራ እጅዋን ወደ ካስማ፤
ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤
በመዶሻውም ሲሣራን መታችው፤
ራሱንም ቸነከረች፤
ጆሮ ግንዱንም በሳች፤ ጐዳችውም።
27በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፤ ወደቀ፤ ተኛ፤
በእግሮችዋ አጠገብ ተፈራገጠ፤
በተፈራገጠበትም በዚያ ተጐሳቍሎ ሞተ።
28የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤
በሰቅሰቅም ዘልቃ፦ ከሲሣራ የተመለሰ እንዳለ አየች፤
ስለምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ?
ስለምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች።
29ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤
እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦
30ምርኮውን ሲካፈል፥
በኀያላኑም ቸብቸቦ ላይ
ወዳጆችን ሲወዳጅ ያገኙት አይደለምን?
የሲሣራ ምርኮ በየኅብሩ ነበረ፤
የኅብሩም ቀለም የተለያየ ነበረ፤
የማረከውም ወርቀ ዘቦ ግምጃ በአንገቱ ላይ ነበረ።
31አቤቱ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤
ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኀይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፤ እንዲሁ ይሁኑ።
ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ