መጽሐፈ መሳፍንት 14
14
ሶምሶን ፍልስጥኤማዊትን ሴት እንዳገባ
1ሶምሶንም ወደ ቴምናታ ወረደ፤ በቴምናታም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ፤ እርስዋም በፊቱ ደስ አለችው። 2ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ፥ “በቴምናታ ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ” አላቸው። 3አባቱና እናቱም፥ “ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች፥ ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለችምን?” አሉት። ሶምሶንም አባቱን፥ “ለዐይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ” አለው። 4አባቱና እናቱም ነገሩ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ አላወቁም፤ እርሱ ከፍልስጥኤማውያን በቀልን ይመልስ ዘንድ ይፈልግ ነበርና። በዚያም ወራት ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ይገዙ ነበር።
5ሶምሶንም፥ አባቱና እናቱም ወደ ቴምናታ ወረዱ፤ በቴምናታም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት። 6የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ አደረ፤ የፍየል ጠቦትን እንደሚጥልም ጣለው፤ በእጁም እንደ ኢምንት ሆነ፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልተናገረም። 7ሂደውም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገሩ፤ ሶምሶንንም በፊቱ ደስ አሰኘችው። 8ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ በአንበሳው አፍ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፤ ማርም ነበረበት። 9ወስዶም በላ፤ እየበላም ሄደ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱም ደረሰ፤ ሰጣቸውም፤ እነርሱም በሉ፤ ማሩንም ከአንበሳው አፍ ውስጥ እንዳወጣው አልነገራቸውም።
10አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ጐበዞችም እንዲሁ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ ሰባት ቀን በዓል አደረገ። 11ከዚህም በኋላ ፈርተው ሠላሳ ሰዎችን በእርሱ ላይ ሾሙ፤ ከእርሱም ጋር ተቀመጡ። 12ሶምሶንም አላቸው፥ “እንቆቅልሽ ልስጣችሁ፤ በሰባቱም በበዓሉ ቀኖች ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤ 13መፍታት ባትችሉ ግን እናንተ ለእኔ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ።” እነርሱም፥ “ምሳሌህን መስልና እንስማህ” አሉት። 14እርሱም፥ “ከበላተኛ መብል ወጣ፤ ከብርቱም ጣፋጭ ወጣ” አላቸው። እስከ ሦስት ቀንም እንቆቅልሹን መፍታት አልቻሉም።
15ከዚህ በኋላ በአራተኛው ቀን የሶምሶንን ሚስት፥ “እንቆቅልሹን እንዲነግርሽ ባልሽን አባብይው፤ አለዚያም አንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፤ ወይስ ወደዚህ የጠራችሁን ልታደኸዩን ነውን?” አሉአት። 16የሶምሶንም ሚስት በፊቱ እያለቀሰችበት፥ “ጠልተኸኛል፤ ከቶም አትወድደኝም፤ ለሕዝቤ ልጆች የነገርኸውን እንቆቅልሽህን አልነገርኸኝምና” አለችው። እርሱም፥ “እነሆ፥ ለአባቴና ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ለአንቺ እነግርሻለሁን?” አላት። 17ሰባቱንም የበዓል ቀን አለቀሰችበት፤ እርስዋም ነዝንዛዋለችና በሰባተኛው ቀን ነገራት። ለሕዝብዋም ልጆች ነገረቻቸው። 18በሰባተኛዪቱም ቀን ፀሐይ ሳትገባ የከተማዪቱ ሰዎች፥ “ከማር የሚጣፍጥ ምንድን ነው? ከአንበሳስ የሚበረታ ማን ነው?” አሉት። ሶምሶንም፥ “በጥጃዬ ባላረሳችሁ ኑሮ የእንቆቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁም ነበር” አላቸው። 19የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ ወረደ፤ ወደ አስቀሎናም ወረደ፤ ከዚያም ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፤ ልብሳቸውንም ገፍፎ እንቆቅልሹን ለነገሩት ሰዎች ሰጠ። ሶምሶንም ተቈጣ፤ ወደ አባቱም ቤት ተመለሰ። 20የሶምሶንም ሚስት ከስር ሚዜው ጋር ተቀመጠች።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ