ትንቢተ ኢሳይያስ 8
8
የኢሳይያስ ልጅ ለሕዝቡ የምርኮ ምልክት እንደ ሆነ
1እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ታላቅ አዲስ ሰሌዳ ወስደህ፦ ‘ቸኩለህ ማርክ፤ ፈጥነህም በዝብዝ’ ብለህ በሰው ብርዕ ጻፍበት። 2የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርያንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮባቸዋልና፤”#“የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮባቸዋልና” የሚለው በዕብ. የለም። 3ወደ ነቢዪቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ስሙን ‘ቸኩለህ ማርክ፤ ፈጥነህም በዝብዝ’ ብለህ ጥራው። 4ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና።”
5እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ 6“እኒህ ሕዝብ በቀስታ በሚሄደው በሰሊሆም ውኃ ቍርጥ ምክርን መከሩ፤ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ያነግሡላቸው ዘንድ ይወዳሉና። 7ስለዚህ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፥ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ ያመጣባቸዋል፤ ወንዙም ሞልቶ ይወጣል፤ በዳሮቻቸውም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤ 8ከይሁዳ ወንድ ሰውን ሁሉ ያጠፋል፤ ኀያላኑንም ይጨርሳል፤ ሰፈሩም በሰፊው ምድርና በሀገሮቻቸው ሁሉ ይሞላል፤” እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።#ዕብ. “እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል፥ እያጥለቀለቀም ያልፋል፥ እስከ አንገቱም ይደርሳል፥ አማኑኤል ሆይ የክንፉ መዘርጋት የሀገርህን ስፋት ትሞላለች” ይላል።
9አሕዛብ ሆይ፥ ዕወቁና ደንግጡ፤ እስከ ምድር ዳርቻም ስሙ፤ ኀያላን! ድል ሁኑ፤ ዳግመኛም ብትበረቱ እንደ ገና ድል ትሆናላችሁ። 10ምክርን ብትመክሩም እግዚአብሔር ምክራችሁን ይለውጣል፤ የተናገራችሁትም ነገር አይሆንላችሁም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና። 11የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ እንዲህ ተናገረኝ፤ በዚህም ሕዝብ መንገድ እንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፤ 12እንዲህም አለኝ፥ “ይህ ሕዝብ፦ ከባድ ነው የሚለውን ሁሉ፦ ከባድ ነው አትበሉ፤ መፈራታቸውንም አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 13ነገር ግን የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን። 14ብታምንበት ይቀድስሃል፤ እንደ ድንጋይ ዕንቅፋትም አያደናቅፍህም፤ እንደሚያድጥ ዓለትም አይሆንብህም፤ ሁለቱ የያዕቆብ ቤቶች ግን በኢየሩሳሌም በወጥመድና በአሽክላ ተይዘው ይኖራሉ።#ዕብ. “እርሱም ለመቅደስ ይሆናል ፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል ፤” ይላል። 15ስለዚህም ከእነርሱ ብዙዎች በእርሱ ይሰናከላሉ፤ ይወድቁማል፤ ይሰበሩማል፤ ይጠመዱማል፤ ይያዙማል።”
16እንዳይማሩአት ሕግን የሚያጠፉአት ሰዎች ያንጊዜ ይገለጣሉ።#ዕብ. “ምስክሩን እሰር ፤ በደቀ መዛሙርቶች መካከል ሕጉን አትም” ይላል። 17ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፥ እተማመንበትማለሁ። 18እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።
19እነርሱም፥ “ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ” ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን? 20ነገሩ እንዲህ አይደለም ይሉ ዘንድ፥ ለእርሱም ግብር እንዳይሰጡ ሕግን ለርዳታ ሰጥቶአልና። 21በዚህም በርግጥ ጽኑ ረኃብ ይመጣባችኋል፤ በተራባችሁም ጊዜ ትጨነቃላችሁ፤ በአለቆችና በመኳንንቱም ላይ ክፉ ትናገራላችሁ፤ ወደ ላይ ወደ ሰማይ ትመለከታላችሁ። 22ወደ ታችም ወደ ምድር ትመለከታላችሁ፤ ድቅድቅ ጨለማንም ታያላችሁ፤ ታላቅ መከራንም ትቀበላላችሁ፤ ትጨነቃላችሁ፤ ትቸገራላችሁም፤ በፊታችሁም ጨለማ ይሆናል፤ አታዩምም፤ በመከራም ያለ ጊዜው እስኪደርስ አይድንም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ