ትንቢተ ኢሳይያስ 54
54
እግዚአብሔር እስራኤልን የወደደበት ፍቅር
1አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፤ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር። 2የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፤ መጋረጃዎችሽንም ዘርጊ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ፤ ካስሞችሽንም ትከዪ። 3እንደ ገናምበቀኝና በግራ ተስፋፊ፤ ዘርሽ አሕዛብን ይወርሳሉና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ታደርጊያለሽና።
4አታፍሪምና አትፍሪ፤ አቷረጂምና አትደንግጪ፤ የዘለዓለም#ዕብ. “የሕፃንነት” ይላል። እፍረትሽንም ትረሺዋለሽ፤ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም። 5ፈጣሪሽ እግዚአብሔር#ዕብ. “ፈጣሪሽ ባልሽ ነው” ይላል። ነው፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም አምላክ ታዳጊሽ ነው፤ እርሱም በምድር ሁሉ እንደዚሁ ይጠራል። 6እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች፥ በልጅነቷም እንደ ተጠላች ሴት የጠራሽ አይደለም፥ ይላል አምላክሽ። 7ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤ በታላቅ ምሕረትም ይቅር እልሻለሁ። 8በጥቂት ቍጣ#ዕብ. “ለቅፅበተ ዐይን” ይላል። ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፤ በዘለዓለም ቸርነት ይቅር እልሻለሁ፥ ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር።
9ከኖኅ ዘመን ውኃ ጀምሮ ይህ ለእኔ ምስክር ነው፤ ቀድሞ ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን እንዳልቈጣት እንደ ማልሁ፥ 10ተራሮችን እንዳልቀሥፋቸው እንዳላፈልሳቸውም፥ ኮረብቶችም እንዳይነዋወጡ እንደ ማልሁ እንዲሁ ከእኔ ዘንድ ያለሽ ይቅርታ አያልቅም፤ የሰላምሽ ቃል ኪዳንም አይጠፋም፤ መሓሪሽ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።
11አንቺ የተቸገርሽ የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን የሚያበሩ አደርጋለሁ፤ መሠረትሽንም የሰንፔር አደርገዋለሁ። 12ግንብሽንም በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም ቢረሌ በተባለ ዕንቍ፥ ዳርቻዎችሽንም በከበረ ዕንቍ እሠራለሁ። 13ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ ልጆችሽም በብዙ ሰላም ይኖራሉ። 14እነሆ፥ በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፤ አትፈሪም፤ ድንጋጤም ወደ አንቺ አይቀርብም። 15እነሆ፥ መጻተኞች በእኔ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ በአንቺም ይማጸናሉ።#ዕብ. “ይሰበሰባሉ ፤ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም ፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ” ይላል። 16እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ እንደሚያናፋ፥ ለሥራውም መሣሪያ እንደሚያወጣ ብረት ሠሪ የፈጠርሁሽ አይደለም፤ እኔ ግን ለመልካም ፈጠርሁሽ እንጂ ለጥፋት አይደለም። 17በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ እንዲከናወን አላደርግም፤ በአንቺ ላይ ለፍርድ የሚነሣውን ድምፅ ሁሉ ታጠፊያለሽ፤ ጠላቶችሽም ሁሉ ይፈረድባቸዋል፤ እግዚአብሔርንም ለሚያገለግሉ ርስት አላቸው፤ ጻድቃኔም ትሆኑኛላችሁ ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 54: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ