የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትን​ቢተ ሐጌ 2

2
1በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2ለይሁዳ አለቃ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁም ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ ስትል ተናገር፦ 3በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምናምን አይደለምን? 4አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል እግዚአብሔር፣ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፥ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱና ሥሩ፥ ይላል እግዚአብሔር፣ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ። 6የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፣ 7አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፣ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 8ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 9ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
10በዳርዮስም በሁለተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ 11የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ካህናቱን ስለ ሕጉ ጠይቅ፣ 12አንድ ሰው የተቀደሰ ሥጋ በልብሱ ዘርፍ ቢይዝ፥ በዘርፉም እንጀራ ወይም ወጥ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ዘይት፥ ወይም ማናቸውም መብል ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይቀደሳልን? ብለህ ካህናቱን ጠይቃቸው፣ ካህናቱም፦ አይሆንም ብለው መለሱ። 13ሐጌም፦ በሬሳ የረከሰ ሰው ከእነዚህ አንዱን ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይረክሳልን? አለ። ካህናቱም፦ አዎን ይረክሳል ብለው መለሱ። 14ሐጌም መልሶ እንዲህ አለ፦ ይህ ሕዝብና ይህ ወገን በፊቴ እንዲሁ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፣ የእጃቸውም ሥራ ሁሉ እንዲሁ ነው፣ በዚያም ያቀረቡት ነገር ርኩስ ነው። 15አሁንም ድንጋይ በድንጋይ ላይ በእግዚአብሔር መቅደስ ሳይነባበር፥ ከዛሬ ጀምራችሁ ወዳለፈው ዘመን ልብ አድርጉ። 16በዚያን ዘመን ሁሉ ሰው ሀያ መስፈሪያ ወዳለበት ምርት በመጣ ጊዜ፥ የተገኘው አሥር መስፈሪያ ብቻ ነው፣ አምሳ ማድጋም ይቀዳ ዘንድ ወደ መጥመቂያው በመጣ ጊዜ፥ የተገኘው ሀያ ብቻ ነው። 17በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ላይ በዋግና በአረማሞ በበረዶም መታኋችሁ፣ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 18ከዛሬው ከዘጠነኛው ወር ከሀያ አራተኛው ቀን ጀምራችሁ የሚመጣውን ዘመን ልብ አድርጉ፣ የእግዚአብሔር መቅደስ መሠረት ከተተከለበት ቀን ጀምሮ ልብ አድርጉ። 19ዘር በጎተራ ገና ይኖራልን? ወይንና በለስ ሮማንና ወይራ አላፈሩም፣ ከዚህች ቀን ጀምሬ እባርካችኋለሁ።
20በወሩ በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21ለይሁዳ አለቃ ለዘሩባቤል ተናገር እንዲህም በል፦ ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ፣ 22የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፥ የአሕዛብንም መንግሥታት ኃይል አጠፋለሁ፣ ሰረገሎችንና የሚቀመጡባቸውንም እገለብጣለሁ፣ ፈረሶችና ፈረሰኞቻቸውም እያንዳንዳቸው በወንድማቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። 23ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፥ በዚያ ቀን እወስድሃለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እኔ መርጬሃለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንደ ቀለበት ማተሚያ አደርግሃለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ