እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “ብዙ፤ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም። አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይ ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱንም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ። ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉንም እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ። ነገር ግን ደመ ነፍስ ያለበትን ሥጋ አትብሉ፤ ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ስለዚያ ደም ፈንታ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሬዋለሁና። እናንተም ብዙ፤ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም።” እግዚአብሔርም ለኖኅ፥ ከእርሱም ጋር ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እኔም እነሆ፥ ቃል ኪዳኔን ከእናንተ ጋር፥ ከእናንተም በኋላ ከዘራችሁ ጋር አጸናለሁ፤ ከእናንተ ጋር ላሉትም፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል። ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።” እግዚአብሔር አምላክም ለኖኅ አለው፥ “በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘለዓለም ትውልድ የማደርገው የቃል ኪዳኔ ምልክት ይህ ነው፤ ቀስቴን በደመና አኖራለሁ፤ የቃል ኪዳኔም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቴ በደመናው ትታያለች፤ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃን አላመጣም። ቀስቴም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር መካከል፥ በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን፥ “በእኔና በምድር ላይ በሚኖር፥ ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያጸናሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው” አለው።
ኦሪት ዘፍጥረት 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 9:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos