እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ መልከ መልካሞች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። እግዚአብሔርም፥ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አይኖርም፤ እነርሱ ሥጋ ናቸውና፤ ዘመናቸውም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናል” አለ። በእነዚያም ወራት ረዓይት በምድር ላይ ነበሩ። ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሰው ሴቶች ልጆች በገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸውን ያስጠሩ ኀያላን ሰዎች ሆኑ። እግዚአብሔርም የሰዎች ክፉ ሥራ በምድር ላይ እንደበዛ፥ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፥ “የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳና አራዊት፥ እስከ ተንቀሳቃሽም፥ እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ፥ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን፥ ካምን ያፌትንም ወለደ። ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተመላች። እግዚአብሔርም ምድርን እንደ ተበላሸች፥ ሥጋን የለበሱ ሁሉም በምድር ላይ መንገዳቸውን እንደ አበላሹ አየ። እግዚአብሔር አምላክም ኖኅን አለው፥ “የሰው ሁሉ ጊዜው በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተመልታለችና፤ እኔም እነሆ፥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ባለ አራት መዓዝን የዕንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፤ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። መርከብዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን። ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመቷም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም፥ ሁለተኛውንም፥ ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ። እኔም እነሆ፥ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል። ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አጸናለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን፥ የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ። ከእንስሳ ሁሉ፥ ከተንቀሳቃሽ አራዊትም ሁሉ፥ ሥጋ ካለው ሁሉ ከአንተ ጋር ትመግባቸው ዘንድ ከሁሉም ሁለት ሁለት ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን። ከወፎች ሁሉ በየወገናቸው፥ ከእንስሳም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ ከሚሳቡ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በየወገናቸው ከአንተ ጋር ይመገቡ ዘንድ ከሁሉም ሁለት ሁለት ወንድና ሴት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። ከሚበላውም የመብል ዓይነት ሁሉ ለአንተ ውሰድ፤ ወደ አንተ ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተ፥ ለእነርሱም መብል ይሆናል።” ኖኅም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፤ እንዲሁ አደረገ።
ኦሪት ዘፍጥረት 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 6:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos