ዮሴፍም ሕልምን አለመ፤ ለወንድሞቹም ነገራቸው። እርሱም አላቸው፥ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ እነሆ፥ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆ፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች በዙርያ ከብበው እነሆ፥ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” ወንድሞቹም፥ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ገዢ ትሆነን ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ሕልምን አየ፤ ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ ደግሞ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ ሕልሙም እንዲህ ነው፦ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ይሰግዱልኝ ነበር።” አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድን ነው? በውኑ እኔና እናትህ፥ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” ወንድሞቹም ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠብቀው ነበር። ወንድሞቹም በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። እስራኤልም ዮሴፍን፥ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና” አለው። እርሱም፥ “እሺ” አለው። እርሱም፥ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። ወደ ኬብሮንም ቆላ ላከው፤ ወደ ሴኬምም መጣ። እነሆም፥ በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውየውም፥ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “ወንድሞችን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ?” አለ። ሰውየውም፥ “ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፤ በዶታይንም አገኛቸው። እነርሱም ወደ እነርሱ ሳይቀርብ ከሩቅ አስቀድመው አዩት፥ ይገድሉትም ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፥ “ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፤ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ሕልሞቹም ምን እንደሚሆኑ እናያለን።” ሮቤልም ይህን ሰማ፤ ከእጃቸውም አዳነው፤ እንዲህም አለ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ።” ሮቤልም፥ “ደም አታፍስሱ፤ በዚች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፤ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። ሮቤልም እንዲህ ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺውን ቀሚሱን ገፈፉት፤ ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ባዶ ነበረ። እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዐይኖቻቸውንም በአነሡ ጊዜ እነሆ፥ ይስማኤላውያን ነጋድያን ከገለዓድ ሲመጡ አዩ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ወደ ግብፅ ሀገርም ሊያራግፉ ይሄዱ ነበር። ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፥ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድን ነው? ኑ፥ ለእነዚህ ይስማኤላውያን እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፤ ወንድማችን ሥጋችን ነውና።” ወንድሞቹም የነገራቸውን ሰሙት። እነዚያ ይስማኤላውያን ነጋዴዎችም ሲያልፉ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ ጐትተው አወጡት፤ ለይስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።
ኦሪት ዘፍጥረት 37 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 37:5-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች