ኦሪት ዘፍጥረት 37
37
ዮሴፍና ወንድሞቹ
1ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት ሀገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ። 2የያዕቆብም ትውልድ እንዲህ ነው። ዮሴፍ ዐሥራ ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው ወደ እስራኤል ያመጣ ነበር።#ግእዙ “ወአምጽኡ ላዕለ ዮሴፍ ውዴተ እኪተ ኀበ አቡሆሙ እስራኤል” ይላል። 3ያዕቆብም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወድደው ነበር፤ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና። በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። 4ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንደሚወድደው በአዩ ጊዜ ጠሉት፤ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።
5ዮሴፍም ሕልምን አለመ፤ ለወንድሞቹም ነገራቸው።#ዕብ. “እነርሱም እንደ ገና በብዙ ተጣሉት” የሚል ይጨምራል። 6እርሱም አላቸው፥ “እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ 7እነሆ፥ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆ፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች በዙርያ ከብበው እነሆ፥ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።” 8ወንድሞቹም፥ “በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ገዢ ትሆነን ይሆን?” አሉት። እንደገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ የበለጠ ጠሉት። 9ደግሞም ሌላ ሕልምን አየ፤ ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ ደግሞ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ ሕልሙም እንዲህ ነው፦ ፀሐይና ጨረቃ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ይሰግዱልኝ ነበር።” 10አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድን ነው? በውኑ እኔና እናትህ፥ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?” 11ወንድሞቹም ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠብቀው ነበር።
ዮሴፍን ወንድሞቹ እንደ ሸጡት
12ወንድሞቹም በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። 13እስራኤልም ዮሴፍን፥ “ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና” አለው። እርሱም፥ “እሺ” አለው። 14እርሱም፥ “ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ” አለው። ወደ ኬብሮንም ቆላ ላከው፤ ወደ ሴኬምም መጣ። 15እነሆም፥ በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውየውም፥ “ምን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። 16እርሱም፥ “ወንድሞችን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ?” አለ። 17ሰውየውም፥ “ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ” አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፤ በዶታይንም አገኛቸው።
18እነርሱም ወደ እነርሱ ሳይቀርብ ከሩቅ አስቀድመው አዩት፥ ይገድሉትም ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። 19አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፥ “ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። 20ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፤ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ሕልሞቹም ምን እንደሚሆኑ እናያለን።” 21ሮቤልም ይህን ሰማ፤ ከእጃቸውም አዳነው፤ እንዲህም አለ፥ “ሕይወቱን አናጥፋ።” 22ሮቤልም፥ “ደም አታፍስሱ፤ በዚች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፤ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት” አላቸው። ሮቤልም እንዲህ ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። 23እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺውን ቀሚሱን ገፈፉት፤ 24ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ባዶ ነበረ።
25እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዐይኖቻቸውንም በአነሡ ጊዜ እነሆ፥ ይስማኤላውያን ነጋድያን ከገለዓድ ሲመጡ አዩ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን፥ ከርቤም ተጭነው ነበር። ወደ ግብፅ ሀገርም ሊያራግፉ ይሄዱ ነበር። 26ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፥ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድን ነው? 27ኑ፥ ለእነዚህ ይስማኤላውያን እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፤ ወንድማችን ሥጋችን ነውና።” ወንድሞቹም የነገራቸውን ሰሙት። 28እነዚያ ይስማኤላውያን ነጋዴዎችም ሲያልፉ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጕድጓድ ጐትተው አወጡት፤ ለይስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።
29ሮቤልም ወደ ጕድጓዱ ተመለሰ፤ እነሆም፥ ዮሴፍን ከጕድጓድ በአጣው ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 30ሮቤልም ወደ ወንድሞቹ ተመልሶ፥ “ብላቴናው በጕድጓድ የለም፤ እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ?” አለ። 31የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፤ የፍየልም ጠቦት አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። 32ብዙ ኅብር ያለበትን ቀሚሱንም ላኩ፤ ወደ አባታቸውም አገቡት፤ እንዲህም አሉት፥ “ይህን ልብስ አገኘን፤ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው?” 33እርሱም ዐውቆ፥ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍን ቦጫጭቆታል” አለ። 34ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፤ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። 35ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ተሰብስበው መጡ። ኀዘኑንም ያስተዉት ዘንድ አባታቸውን ማለዱት። ኀዘኑንም መተውን እንቢ አለ፥ እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ልጄ ወደ መቃብር እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። 36እነዚያ ይስማኤላውያን#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “ምድያማውያን” ይላል። ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 37: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ