ኦሪት ዘፍጥረት 35
35
እግዚአብሔር ያዕቆብን እንደ ባረከው
1እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፥ “ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፤ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጥሁልህ ለእኔ መሥውያን ሥራ።” 2ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ፥ “ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶች አማልክትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ንጹሓንም ሁኑ፤ ልብሳችሁንም እጠቡ፤ 3ተነሡና ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ቀን ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው፥ ከመከራም አድኖ ላሻገረኝ ለእግዚአብሔር መሠውያን እንሥራ።” 4በእጃቸው ያሉትንም እንግዶች አማልክት ሁሉ፥ በጆሮአቸውም ያሉትን ጉትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴቄም አጠገብ ካለችው ዛፍ በታች ቀበራቸው። እስከ ዛሬም ድረስ አጠፋቸው። 5እስራኤልም ከሴቄም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም መፍራት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፤ የእስራኤልንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። 6ያዕቆብም እርሱ፥ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት። 7በዚያም መሠውያዉን ሠራ፤ የዚያንም ቦታ ስም ቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ከዔሳው ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና። 8የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፤ ከቤቴል በታች ባላን በሚባል ዛፍ ሥርም ተቀበረች፤ ያዕቆብም ስሙን “የልቅሶ ዛፍ” ብሎ ጠራው።
9እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደገና በሎዛ ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም ባረከው። 10እግዚአብሔርም አለው፥ “ስምህ ያዕቆብ አይባል፤ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ” ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11እግዚአብሔርም አለው፥ “አምላክህ እኔ ነኝ፤#ዕብ. “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ” ይላል። ብዛ፤ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፤ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። 12ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ።” 13እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። 14ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፤ ዘይትንም አፈሰሰበት። 15ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ “ቤቴል” ብሎ ጠራው።
የራሔል ሞት
16ያዕቆብም ከቤቴል ተጓዘ፤ በጋዲር ግንብ አጠገብ ድንኳን ተከለ፤ ወደ ኤፍራታም ለመድረስ በቀረበ ጊዜ ራሔልን ምጥ ያዛት፤ በምጡም ተጨነቀች። 17በምጥ ሳለችም አዋላጂቱ፥ “አትፍሪ ይህኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንልሻልና” አለቻት። 18ከዚያም በኋላ ነፍስዋ ልትወጣ ደረሰች፤ ሞትዋ በእርሱ ሆኖአልና ስሙን የጭንቀቴ ልጅ ብላ ጠራችው ፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። 19ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታም በምትወስድ መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት። 20ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርስዋም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ትባላለች። 21ከዚህም በኋላ እስራኤል በዚያች ምድር ሳለ ሮቤል ሄደ፤ ከአባቱ ከያዕቆብ ዕቅብት ከባላ ጋርም ተኛ፤ እስራኤልም ሰማ። በፊቱም ክፉ ነገር ሆነ።
የያዕቆብ ልጆች
(1ዜ.መ. 2፥1-2)
22የያዕቆብም ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው፤ 23የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤ 24የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ 25የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤ 26የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው።
የይስሐቅ ሞት
27ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ፥ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት በአርባቅ ከተማ ወደምትገኘው ወደ መምሬ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። 28የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። 29ይስሐቅም ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተጨመረ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 35: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ