እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። እግዚአብሔር አምላክም በኤዶም በስተምሥራቅ ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ደግሞ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያሳየውንና የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ። ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤዶም ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለዐራት መዓዝን ይከፈል ነበር። የአንደኛው ወንዝ ስም ኤፌሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል። የዚያችም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው። በዚያም የሚያበራ ዕንቍና የሚያብረቀርቅ ዕንቍ አለ። የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል፤ የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሶር ላይ የሚሄድ ነው። አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም፥ ይጠብቃትም ዘንድ በኤዶም ገነት አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም አዳምን እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” እግዚአብሔር አምላክም አለ፥ “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ።” እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ደግሞ ከምድር ፈጠረ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ስሙ ያው ሆነ። አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው። ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቀላፋም ፤ ከጎኑም አጥንቶች አንድ አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ መላው።
ኦሪት ዘፍጥረት 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 2:7-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos