ኦሪት ዘፀአት 6
6
የእስራኤል ከግብፃውያን አርነት መውጣት እንደ ተረጋገጠ
1እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋልና፥ በተዘረጋችም ክንድ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።” 2እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3ለአብርሃምም፥ ለይስሐቅም፥ ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። 4የነበሩባትንም የከነዓንን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። 5ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።” 6ስለዚህም ፈጥነህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፤ ከባርነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፤ 7ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፤ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ እጄን ወደ ዘረጋሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” 9ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ፥ ከሥራቸውም ክብደት የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም።
10እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11“ግባ፤ የእስራኤልን ልጆች ከሀገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው።” 12ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? እኔም አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም” ብሎ ተናገረ። 13እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው።
የሙሴና የአሮን ትውልድ
14የአባቶቻቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች ሄኖኅ፥ ፍሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ትውልድ ናቸው። 15የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ አኡድ፥ ያኪን፥ ሱሐር፥ የፊኒቃዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ትውልድ ናቸው። 16እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 17የጌድሶንም ልጆች በየአባታቸው ወገን ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው።
18የቀዓትም ልጆች እንበረም፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አምብራም” ይላል። ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው። 19የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሐሙሲ ናቸው። እነዚህም እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ትውልድ ናቸው። 20እንበረምም የአባቱን ወንድም ልጅ ዮካብድን አገባ፤ አሮንንና ሙሴን፥ እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 21የይስዓርም ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው። 22የዑዝኤልም ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልሳፋን፥ ሴትሪ ናቸው። 23አሮንም የአሚናዳብን ልጅ የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ። እርስዋም ናዳብንና አብዩድን፥ አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት። 24የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ትውልድ ናቸው። 25የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፋትኤል ልጆች ሚስትን አገባ፤ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህም በየወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው። 26እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር፥ “ከግብፅ ምድር ከሠራዊቶቻቸው ጋር የእስራኤልን ልጆች አውጡ” ያላቸው ናቸው። 27እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህም ሙሴና አሮን ናቸው።
እግዚአብሔር ለሙሴና አሮን የሰጠው ትእዛዝ
28እግዚአብሔርም በግብፅ ሀገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤ 29እግዚአብሔር ሙሴን፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር” ብሎ ተናገረው። 30ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል?” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ