እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ እኔ የፈርዖንንና የሹሞቹን ልብ አጽንቼአለሁና፥ ተአምራቴ በእነርሱ ላይ በትክክል ይመጣ ዘንድ፤ በግብፃውያንም ላይ የተዘባበትሁትን ሁሉ፥ ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጆቻችሁና በልጅ ልጆቻችሁ ጆሮች ትነግሩ ዘንድ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፤ አሉትም፥ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ማፈርን እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ፥ ነገ በዚህ ጊዜ በተራራዎችህ ሁሉ ላይ አንበጣን አመጣለሁ፤ የምድሩንም ፊት ይሸፍናል፤ ምድሩን ለማየት አይቻልም፤ ከበረዶውም ተርፎ በምድር ላይ የቀረላችሁን ትርፍ ሁሉ ይበላል፤ ያደገላችሁንም የእርሻውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ ቤቶችህም የሹሞችህም ሁሉ ቤቶች፥ የግብፃውያን ሁሉ ቤቶች በእርሱ ይሞላሉ፤ አባቶችህ፥ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያላዩት ነው።” ሙሴም ተመልሶ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። የፈርዖንም ሹሞች፥ “ይህ ሰው እስከ መቼ እንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ፤ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን?” አሉት። ሙሴንና አሮንንም ወደ ፈርዖን ጠሩአቸው፤ ፈርዖንም እንዲህ አላቸው፥ “ሂዱ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን ከእናንተ ጋር የሚሄዱት እነማን ናቸው?” ሙሴም አለው፥ “እኛ ከታናናሾቻችንና ከሽማግሌዎቻችን፥ ከወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ጋር እንሄዳለን፤ በጎቻችንንና ላሞቻችንንም እንወስዳለን። የአምላካችን የእግዚአብሔር በዓል ነውና።” ፈርዖንም አላቸው፥ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ እነሆ፥ እናንተን ስለቅ ልጆቻችሁንም መልቀቅ አለብኝን? ክፉ ነገር እንደሚገጥማችሁ ዕወቁ። እንዲህም አይደለም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱ፤ ይህን ፈልጋችኋልና እግዚአብሔርን አምልኩ” አላቸው። ሙሴንና አሮንንም ከፈርዖን ፊት አስወጡአቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በግብፅ ሀገር ላይ እጅህን ዘርጋ፤ አንበጣም በምድር ላይ ይወጣል፤ ከበረዶውም የተረፈውን የምድር ቡቃያ ሁሉና የዛፉን ፍሬ ሁሉ ይበላል።” ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም የደቡብን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱንም ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የደቡብ ነፋስ አንበጣን አመጣ። አንበጣም በግብፅ ሀገር ሁሉ ላይ ወጣ፤ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጠ፤ እጅግም ብዙና ጠንካራ ነበር፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፤ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም። የምድሩንም ፊት ፈጽሞ ሸፈነው፤ ሀገሪቱም ጠፋች፤ የሀገሪቱን ቡቃያ ሁሉ ከበረዶውም የተረፈውን፥ በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በላ፤ ለምለም ነገር በዛፎች ላይ፥ በእርሻውም ቡቃያ ሁሉ ላይ በግብፅ ሀገር ሁሉ አልቀረም።
ኦሪት ዘፀአት 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 10:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች