ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3
3
የጳውሎስ መታሰር
1ስለዚህ አሕዛብ ሆይ ስለ እናንተ እኔ ጳውሎስ የክርስቶስ እስረኛው ነኝ። 2ስለ እናንተ የሰጠኝን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ስጦታ#ግሪኩ “መጋቢነት” ይላል። ሰምታችኋል። 3አስቀድሞ በጥቂቱ እንደ ጻፍሁላችሁ ይህን ምሥጢር ገልጦ አሳይቶኛልና። 4ይህንም በምታነቡበት ጊዜ፥ የክርስቶስን ምሥጢር ማስተዋሌን ለማወቅ ትችላላችሁ። 5በሌላ ዘመን ለሰው ልጆች ያልተገለጠ ዛሬ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ለነቢያቱ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተገለጠ፥ 6#ቈላ. 1፥26-27። አሕዛብን ወራሾቹና አካሉ ያደርጋቸው ዘንድ፥ በወንጌልም ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ተስፋ አንድ ይሆኑ ዘንድ። 7በኀይሉ አጋዥነት እንደ ሰጠኝ እንደ ጸጋው ስጦታ መጠን እኔ መልእክተኛና አዋጅ ነጋሪ የሆንሁለት፥ 8ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ አስተምር ዘንድ ይህን ጸጋ ሰጠኝ። 9ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረ የዚህ ምሥጢር ሥርዐትንም ለሁሉ እገልጥ ዘንድ፤ 10ብዙ ልዩ ልዩ የሆነች የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ 11ዓለም ሳይፈጠር የወሰናት፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም የፈጸማት፥ 12እኛ ጸጋንና ባለሟልነትን ያገኘንበት፥ በሃይማኖት ወደሚገኘው ተስፋም ያደረሰበት፤ 13ስለዚህም ስለ እናንተ ለክብራችሁ የምታገኘኝን መከራዬን ቸል እንዳይላት እግዚአብሔርን እማልደዋለሁ።#ምዕ. 3 ቍ. 13 “... ስለ እናንተ ስላለ መከራዬ እንዳትታክቱ እለምናችኋለሁ ክብራችሁ ነውና” ይላል።
የጳውሎስ ጸሎት
14ስለዚህም በልቡናዬ ተንበርክኬ ለአብ እሰግዳለሁ። 15በሰማይና በምድር ያሉ ነገዶች ሁሉ ለሚጠሩት ለእርሱ፤ 16እንደ ጌትነቱ ምላት ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ያጸናችሁ ዘንድ። 17በልባችሁ ውስጥ በፍቅር ሥር መሠረታችሁ የጸና ሲሆን ክርስቶስ በሃይማኖት በሰው ውስጥ ያድራልና። 18ስፋቱና ርዝመቱ፥ ምጥቀቱና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ለማስተዋል ትችሉ ዘንድ፥ 19የክርስቶስን ፍቅር ለመረዳት፥ በእግዚአብሔር ፍጹምነት በሁሉ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ።
20በከሃሊነቱ እንደ ረዳን መጠን፥ የምናስበውንና የምንለምነውን ሁሉ ትሠሩ ዘንድ፥ ታበዙም ዘንድ ሊያጸናችሁ ለሚችል፥ 21ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ፥ በትውልድ ሁሉ ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን።
Currently Selected:
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ