ስለ እናንተ እና በሎዶቅያ ስላሉ፥ ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ምእመናን ሁሉ ምን ያህል እንደምጋደል ልታውቁ እወዳለሁ። ይኸውም ልቡናቸው ደስ ይለው ዘንድ፥ ትምህርታቸውም በማወቅ፥ በፍቅርና ፍጹምነት ባለው ባለጸግነት፥ በጥበብና በሃይማኖት፥ ስለ ክርስቶስም የሆነውን የእግዚአብሔርን ምክር በማወቅ ይጸና ዘንድ ነው። የተሰወረ የጥበብና የምክር መዝገብ ሁሉ በእርሱ ዘንድ አለ። ይህንም የምላችሁ በሚያባብል ነገር የሚያስታችሁ እንዳይኖር ነው። እኔ በሥጋ ከእናንተ ዘንድ ባልኖርም እንኳን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ እነሆ ጠባያችሁንና ሥርዐታችሁን፥ በክርስቶስም ያለ የእምነታችሁን ጽናት ስለ አየሁ ደስ ይለኛል። እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተቀበላችሁት፥ በእርሱ ተመላለሱ። በእርሱ ተመሥርታችሁ ታነጹ፤ በምስጋናው ትበዙ ዘንድ፥ በተማራችሁት ሃይማኖት ጽኑ። ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥርዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ ተጠንቀቁ። በእርሱ ፍጹም መለኮቱ በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። እናንተም በእርሱ ፍጹማን ሁኑ፤ እርሱ ለአለቅነት ሁሉና ለሥልጣን ሁሉ ራስ ነውና። የኀጢአትን ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል። እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ። ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈውን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው። አለቆችንና ገዢዎችን በመግፈፉ በግልጥ አሳያቸው፤ ራቁቱን በመሆኑም አሳፈራቸው። እንግዲህ በመብልም ቢሆን፥ በመጠጥም ቢሆን፥ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን፥ በመባቻም ቢሆን፥ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ። ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ፥ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር። ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት፥ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት፥ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት፥ በሚሞላበትም በራስ አይጸናም።
ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች