እኛ ግን በመርከብ ሆነን ወደ አሶስ ሄድን፤ ከዚያ ጳውሎስን ልንቀበለው እንሻ ነበርና፤ እንደዚሁ በእግር እንደሚመጣ ነግሮን ነበርና ተቀበልነው። አሶስም ደረስን፤ በመርከብም ይዘነው ወደ ሚጢሊኒ ሄድን። በማግሥቱም ከዚያ ወጥተን በኪዮስ ፊት ለፊት ደረስን፤ በማግሥቱም ወደ ሳሞስ አለፍን፤ በትሮጊሊዮም ተቀመጥን፤ ከዚህ ቀን በኋላም ወደ መሊጡ ደረስን። ጳውሎስም በእስያ እንዳይዘገይ በኤፌሶን በኩል ሊሄድ ቈርጦ ነበር፤ የሚቻለውም ቢሆን ለበዓለ ኀምሳ ኢየሩሳሌም ለመድረስ ቸኵሎ ነበርና። ከመሊጡም የቤተ ክርስቲያንን ቀሳውስት ይጠሩአቸው ዘንድ ወደ ኤፌሶን ላከ። ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፥ “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ዘንድ እንደ ተቀመጥሁ እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔርን እያገለገልሁ በፍጹም መከራና በልቅሶ ከአይሁድም ሴራ የተነሣ በደረሰብኝ ፈተና እየተጋደልሁ፥ በጉባኤም ሆነ በቤት ስነግራችሁና ሳስተምራችሁ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳን አላስቀረሁባችሁም። ወደ እግዚአብሔር መመለስንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለአረማውያን እየመሰከርሁ፤ አሁንም እነሆ በመንፈስ ታሥሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ ነገር ግን በዚያ የሚያገኘኝን አላውቅም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ በየከተማው መከራና እስራት ይጠብቅሃል ብሎ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ወንጌል እንዳስተምር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልሁትን ሩጫዬን እንድጨርስና መልእክቴንም እንድፈጽም ነው እንጂ ለሰውነቴ ምንም አላስብላትም። አሁንም እነሆ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ እናንተ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንደማታዩኝ እኔ ዐውቄአለሁ። እኔ ከሁላችሁም ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ እነሆ ዛሬ በዚች ሌሊት እመሰክርላችኋለሁ። ከእግዚአብሔር ምክር ሁሉ የሰወርኋችሁና ያልነገርኋችሁ የለም። አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከእኔ በኋላ ለመንጋዪቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኵላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ። ደቀ መዛሙርትንም ወደ እነርሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ከእናንተ መካከል ይነሣሉ። ስለዚህም ትጉ፤ እኔ ሁላችሁንም ሳስተምር ሦስት ዓመት ሙሉ ሌትም ቀንም እንባዬ እንዳልተገታ ዐስቡ። አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያንጻችሁ፥ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ። ወርቅም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን፥ ልብስም ቢሆን ከእናንተ ከአንዱ ስንኳ አልተመኘሁም። እነዚህም እጆች ለምሻው ነገርና ከእኔም ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ። በድካማችንና በሥራችን ነዳያንን እንቀበላቸው ዘንድ እንደሚገባን ይህን አስተምሬአችኋለሁ፤ ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው’ ያለውንም የጌታችንን የኢየሱስን ቃል ዐስቡ።” ይህንም ከአለ በኋላ ተንበርክኮ አብረውት ካሉት ሁሉ ጋር ጸለየ። ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ሳሙት። ይልቁንም “ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩትም” ስለ አላቸው እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት።
የሐዋርያት ሥራ 20 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 20:13-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች