ይህም ከተፈጸመ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ በልቡ ዐሰበ፥ “እዚያም ከደረስሁ በኋላ ሮሜን ላያት ይገባኛል” አለ። ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና አርስጦስን ወደ መቄዶንያ ላከ፤ እርሱ ራሱ ጳውሎስ ግን ብዙ ቀን በእስያ ተቀመጠ። በዚያም ወራት ስለዚህ ትምህርት ብዙ ሁከት ሆነ። በዚያም ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ለአርጤምስም ከብር የቤተ መቅደስ ምስል ይሠራ ነበር፤ አንጥረኞችንም እያሠራ ብዙ ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር። አንጥረኞችንና ይህን የመሰለውን ሥራ የሚሠሩትንም ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ጥቅም የምናገኘው በዚህ ሥራችን እንደ ሆነ እናንተ ታውቃላችሁ። አሁን ግን እንደምታዩትና እንደምትሰሙት ይህ ጳውሎስ ኤፌሶንን ብቻ ሳይሆን መላውን እስያን አሳተ፤ ብዙ ሕዝብንም መለሰ፤ በሰው እጅ የሚሠሩትንም ሁሉ አማልክት አይደሉም አላቸው። አሁን የምንቸገር በዚህ ነገር ብቻ አይደለም፤ እስያና መላው ዓለም የሚያመልካት የታላቋ የአርጤምስም መቅደስ ክብር ይቀራል፤ ገናናነቷም ይሻራል።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ተቈጡና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፥ “የኤፌሶን አርጤምስ ክብርዋ ታላቅ ነው” አሉ። ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ የመቄዶንያን ሰዎች የጳውሎስን ወዳጆች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስንም ከእነርሱ ጋር እየጐተቱበአንድነት ወደ ጨዋታው ቦታ ሮጡ። ጳውሎስም ወደ አሕዛብ መካከል ሊገባ ወድዶ ነበር፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። ከእስያም የሆኑ ታላላቆች ወዳጆቹ ወደ ጨዋታው ቦታ እንዳይገባ ልከው ማለዱት። በዚያም በጨዋታው ቦታ የነበሩ ሰዎች እየጮኹ ቈዩ፤ በሌላም ቋንቋ የሚጮሁ ነበሩ፤ በጉባኤው ታላቅ ድብልቅልቅ ሆኖ ነበርና፤ ከእነርሱ የሚበዙት ግን በምን ምክንያት እንደ ተሰበሰቡ አያውቁም ነበር። በዚያ የነበሩ አይሁድም እስክንድሮስ የሚባል አይሁዳዊ ሰውን ከመካከላቸው አስነሡ፤ እርሱም ተነሥቶ በእጁ ምልክት ሰጠና ለሕዝቡ ሊከራከርላቸው ወደደ። አይሁዳዊ እንደሆነም ባወቁ ጊዜ “የኤፌሶን አርጤምስ ክብርዋ ታላቅ ነው” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ሁሉም በአንድ ድምፅ ጮሁ። ከዚህም በኋላ የከተማው ጸሓፊ ተነሥቶ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ ስሙ፤ የኤፌሶን ከተማ ታላቂቱን አርጤምስንና ከሰማይ የወረደውን ጣዖትዋን እንደምትጠብቅ የማያውቅ ማነው? ስለዚህም እርስዋን መቃወም የሚቻለው ያለ አይመስለኝም፤ አሁንም ይህን በጠብና በክርክር ሳይሆን በቀስታ ልናደርገው ይገባናል። የአማልክትን ቤት ያልዘረፉትንና በአማልክቶቻችን ላይ ክፉ ቃልን ያልተናገሩትን እነዚህን ሰዎች እነሆ ወደ እዚህ አምጥታችኋቸዋል። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉ አንጥረኞች ግን በማንም ላይ ጠብ እንዳላቸው እርስ በርሳቸው ይከራከሩ፤ እነሆም በከተማው ውስጥ ፍርድ ቤት አለ፤ ዳኞችም አሉ። ነገር ግን ይህ የምትከራከሩበት ነገር ሌላ ከሆነ በሕግ ሸንጎ ይፈታል። ዛሬም በደል ሳይኖር በአመጣችሁብን ክርክር እኛ እንቸገራለንና ስለዚህ ክርክር የምንወቃቀሰው ነገር የለም፥” ይህንም ብሎ ሸንጎውን ፈታ።
የሐዋርያት ሥራ 19 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 19:21-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች