ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊም አገኘ፤ የትውልድ ሀገሩም ጳንጦስ ነው፤ እርሱም ከጥቂት ወራት በፊት ከኢጣልያ ተሰዶ መጣ፤ ሚስቱ ጵርስቅላም አብራው ነበረች፤ ቀላውዴዎስ አይሁድ ከሮም እንዲሰደዱ አዝዞ ነበርና ወደ እነርሱ መጣ። ሥራቸው አንድ ስለ ነበረ ድንኳን ሰፊዎችም ስለ ነበሩ ከእነርሱ ጋር አብሮ ኖረ፤ በአንድነትም ይሠሩ ነበር። ጳውሎስም በየሰንበቱ በምኵራብ ይከራከራቸው ነበር፤ አይሁድንና አረማውያንንም ያሳምናቸው ነበር። ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ቃሉን በማስተማር ይተጋ ነበር። እነርሱም በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፥ “እንግዲህ እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ነው፤ ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው። ከዚያም አልፎ ስሙ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚፈራ ሰው ቤት ገባ፤ ቤቱም በምኵራብ አጠገብ ነበር። የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከነቤተ ሰቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ፤ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙዎች ሰምተው አምነው ተጠመቁ። ጌታችንም ጳውሎስን በሌሊት ራእይ እንዲህ አለው፥ “አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር፥ ዝምም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም ሊጐዳህ የሚነሣብህ የለም፤ በዚች ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና።” ጳውሎስም የእግዚአብሔርን ቃል እየአስተማራቸው ዓመት ከስድስት ወር በቆሮንቶስ ተቀመጠ። ጋልዮስም የአካይያ አገረ ገዢ በሆነ ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ሸንጎም አመጡት። እንዲህም አሉት፥ “ይህ ሰው ኦሪትን በመቃወም እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ ሰዎችን ያባብላል።” ጳውሎስም ይመልስላቸው ዘንድ አፉን ሊከፍት ወድዶ ሳለ አገረ ገዢው ጋልዮስ መልሶ አይሁድን እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ አይሁድ ሆይ፥ የበደላችሁ በደል ቢኖር፥ ወይም ሌላ በደል ቢኖርበት አቤቱታችሁን በሰማሁና ባከራከርኋችሁ ነበር። ስለ ትምህርትና ስለ ስሞች፥ ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን ለራሳችሁ ዕወቁ፤ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ልሰማ አልፈቅድም።” ከሸንጎውም አባረራቸው። አረማውያንም ሁሉ የምኵራቡን አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎ ፊት ደበደቡት፤ የእርሱም ነገር ጋልዮስን ምንም አላሳዘነውም። ጳውሎስም እንደ ገና በወንድሞቹ ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጠ፤ በሰላምም ሸኙትና ወደ ሶርያ በባሕር ተጓዘ፤ ጵርስቅላና አቂላም አብረውት ነበሩ፤ ስእለትም ነበረበትና በክንክራኦስ ራሱን ተላጨ።
የሐዋርያት ሥራ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 18:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች