የሐዋርያት ሥራ 18
18
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር እንደ ተገናኘ
1ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። 2አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊም አገኘ፤ የትውልድ ሀገሩም ጳንጦስ ነው፤ እርሱም ከጥቂት ወራት በፊት ከኢጣልያ ተሰዶ መጣ፤ ሚስቱ ጵርስቅላም አብራው ነበረች፤ ቀላውዴዎስ አይሁድ ከሮም እንዲሰደዱ አዝዞ ነበርና ወደ እነርሱ መጣ። 3ሥራቸው አንድ ስለ ነበረ ድንኳን ሰፊዎችም ስለ ነበሩ ከእነርሱ ጋር አብሮ ኖረ፤ በአንድነትም ይሠሩ ነበር። 4ጳውሎስም በየሰንበቱ በምኵራብ ይከራከራቸው ነበር፤ አይሁድንና አረማውያንንም ያሳምናቸው ነበር።
5ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ቃሉን በማስተማር ይተጋ ነበር። 6እነርሱም በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፥ “እንግዲህ እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ነው፤ ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው። 7ከዚያም አልፎ ስሙ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚፈራ ሰው ቤት ገባ፤ ቤቱም በምኵራብ አጠገብ ነበር። 8የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከነቤተ ሰቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ፤ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙዎች ሰምተው አምነው ተጠመቁ። 9ጌታችንም ጳውሎስን በሌሊት ራእይ እንዲህ አለው፥ “አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር፥ ዝምም አትበል፤ 10እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም ሊጐዳህ የሚነሣብህ የለም፤ በዚች ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና።” 11ጳውሎስም የእግዚአብሔርን ቃል እየአስተማራቸው ዓመት ከስድስት ወር በቆሮንቶስ ተቀመጠ።
12ጋልዮስም የአካይያ አገረ ገዢ በሆነ ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ሸንጎም አመጡት። 13እንዲህም አሉት፥ “ይህ ሰው ኦሪትን በመቃወም እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ ሰዎችን ያባብላል።” 14ጳውሎስም ይመልስላቸው ዘንድ አፉን ሊከፍት ወድዶ ሳለ አገረ ገዢው ጋልዮስ መልሶ አይሁድን እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ አይሁድ ሆይ፥ የበደላችሁ በደል ቢኖር፥ ወይም ሌላ በደል ቢኖርበት አቤቱታችሁን በሰማሁና ባከራከርኋችሁ#“ባከራከርኋችሁ” የሚለው በግሪኩ የለም። ነበር። 15ስለ ትምህርትና ስለ ስሞች፥ ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን ለራሳችሁ ዕወቁ፤ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ልሰማ አልፈቅድም።” 16ከሸንጎውም አባረራቸው። 17አረማውያንም ሁሉ የምኵራቡን አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎ ፊት ደበደቡት፤ የእርሱም ነገር ጋልዮስን ምንም አላሳዘነውም።
18 #
ዘኍ. 6፥18። ጳውሎስም እንደ ገና በወንድሞቹ ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጠ፤ በሰላምም ሸኙትና ወደ ሶርያ በባሕር ተጓዘ፤ ጵርስቅላና አቂላም አብረውት ነበሩ፤ ስእለትም ነበረበትና በክንክራኦስ ራሱን ተላጨ። 19ወደ ኤፌሶንም ደረሱ፤ በዚያም ተዋቸውና እርሱ ብቻውን ወደ ምኵራብ ገብቶ አይሁድን ተከራከራቸው። 20እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲሰነብት ማለዱት፤ ነገር ግን አልወደደም። 21ከዚህም በኋላ በሚሸኙት ጊዜ፥ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንደገና እመለሳለሁ፤ አሁን ግን የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም ላደርግ እወዳለሁ” አላቸው፤ ከኤፌሶንም በመርከብ ሄደ።
22ወደ ቂሳርያም ደረሰ፤ ከዚያም ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ሄደ። 23ጥቂት ቀንም ተቀመጠ፤ ከዚያም ወጥቶ በገላትያና በፍርግያ በኩል በተራ እየዞረ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም አጸናቸው።
24በእስክንድርያም የሚኖር፥ ንግግር የሚችልና መጽሐፍን የሚያውቅ አጵሎስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን መጣ። 25እርሱም የእግዚአብሔርን መንገድ የተማረ ነበር፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ሊያስተምርና ሊመሰክር ከልቡ የሚተጋ ነበር፤ ነገር ግን የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ተጠምቆ ነበር። 26እርሱም በምኵራብ በግልጥ ይናገር ጀመር፤ ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ ወደ ማደሪያቸው ወስደው ፍጹም የእግዚአብሔርን መንገድ አስረዱት። 27ወደ አካይያም ሊሄድ በወደደ ጊዜ ወንድሞች አጽናኑት፤ እንዲቀበሉትም ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ ወደ እነርሱም በደረሰ ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ላመኑት ብዙ አስተማራቸው፤ ትልቅ ርዳታም ረዳቸው። 28ተሰብስበው ሳሉም በሕዝቡ ሁሉ ፊት አይሁድን በግልጥ እጅግ ይከራከራቸው ነበር፤ ስለ ኢየሱስም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት ማስረጃ ያመጣላቸው ነበር።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ