አንፊጶልና አጶሎንያ ወደሚባሉ ሀገሮችም ሄዱ፤ የአይሁድ ምኵራብ ወደ አለበት ወደ ተሰሎንቄም ደረሱ። ጳውሎስም እንደ አስለመደው ወደ እነርሱ ገብቶ ሦስት ሳምንት ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ሲከራከራቸው ሰነበተ። ክርስቶስ እንዲሞት ከሙታንም ተለይቶ እንዲነሣ፥ እየተረጐመና እየአስተማራቸው፥ “ይህ እኔ የነገርኋችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” ይል ነበር። ከእነርሱና ከደጋጎች አረማውያንም ብዙ ሰዎች፥ ከታላላቆች ሴቶችም ጥቂቶች ያይደሉ አምነው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ሆኑ። የማያምኑ አይሁድ ግን ቀኑባቸው፤ ከገበያም ክፉዎች ሰዎችን አምጥተው፥ ሰዎችንም ሰብስበው ሀገሪቱን አወኳት፤ ፈለጓቸውም፤ የኢያሶንን ቤትም በረበሩ፤ ወደ ሕዝቡም ሊያወጧቸው ሽተው ነበር። በአጧቸውም ጊዜ ኢያሶንን ጐተቱት፤ በዚያም የነበሩትን ጓደኞች ጭምር ወደ ሹሞቹ ወሰዱአቸው፤ እየጮኹም እንዲህ ይሉ ነበር፥ “ዓለምን የሚያውኳት እነዚህ ናቸው፤ ወደዚህም መጥተዋል። ይህ ኢያሶንም ተቀበላቸው፤ እነርሱም በቄሣር ላይ የወንጀል ሥራ ይሠራሉ፤ ሌላ ሕግንም ያስተምራሉ፤ ኢየሱስም ሌላ ንጉሥ ነው” ይላሉ። ሕዝቡና የከተማው ሹሞችም ይህን በሰሙ ጊዜ ታወኩ። ከኢያሶንና ከጓደኞቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው።
የሐዋርያት ሥራ 17 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 17
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 17:1-9
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች